Sunday, September 22, 2024
spot_img

ሱዳን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ላይ የባለቤትነት ጥያቄ አለኝ ማለቷ አስነዋሪ መሆኑን አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሚያዝያ 27፣ 2013 ― ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በሚካሄድበት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ላይ የባለቤትነት ጥያቄ አለኝ ማለቷ አስነዋሪ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባዩ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባዩ ሱዳን የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የራሷ ግዛት መሆኗን መናገሯን በመጥቀስ፣ የድንበር ጉዳይን ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ በዓባይ ወንዝ ላይ ከተደረገው የቅኝ ገዥዎች ስምምነት ማገናኘቷ አሳዛኝ ነው ያሉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በምዕራብ በኩል ከሱዳን ጋር የምትዋሰንበት ድንበር አሁን ያለው ሳይሆን፣ ከዚያም ሊያልፍ ይችል እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ትላንት በሰጡት በሳምንታዊ ጋዜጣዊ መግለጫቸው፣ የኢትዮጵያን ታጋሽነትና መልካምነት እንደ ድክመት በመቁጠር ቤኒሻንጉል ጉምዝ የእኔ መሬት ስለሆነ ይገባኛል ብሎ መጠየቅ ‹‹አስነዋሪ›› ድርጊት ነው ብለዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በሱዳን በኩል እየተኬደበት ላለው ያልተረጋገጠ ጠበኛ የቅስቀሳ ዘመቻና ወረራ መንግሥት በተደጋጋሚ ጥሪ ማቅረቡን፣ የድንበር ጉዳይ በድንበር ኮሚሽኑ ብቻ እንዲታይ እየተጠየቀ ሱዳን ቤኒሻንጉል ጉምዝ የእኔ ነው ማለቷ ፍፁም ቅጥ ያጣ ድርጊት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ጉዳይ ከህዳሴው ግድብም ሆነ ከድንበር ጉዳይ ጋር እንደማይገናኝ የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፣ ሱዳን አንድነትን የሚፃረር ፍላጎት ማሳየቷ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በከፍተኛ ሁኔታ ይጋፋል ብለዋል፡፡

አክለውም ኢትዮጵያ የአፍሪካንም ሆነ የዓለም አቀፍ ሕጎችን በማክበር የምትታወቅ ምሥጉን አገር ነች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img