Friday, November 22, 2024
spot_img

እዩ ጩፋ በቤተክርስትያኑ የተገኙ የመከላከያ አባላትን ወታደራዊ የደንብ ልብሱን ለብሳችሁ ኑ አላልንም ሲል ምላሽ ሰጠ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 26፣ 2013 ― የአገረ መከላከያ የሠራዊት አባላቱን የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ክብር ባልጠበቀ መልኩ፣ በቪዲዮና ፎቶ ቀርጾ በአደባባይ እንዲሰራጭ በማድረጉ እዩ ጩፋ ላይ ክስ እመሰርታለሁ ማለቱ ይታወሳል።

እዩ ጩፋ የአገር መከላከያ ሠራዊት ስላወጣው መግለጫ በቪዲዮ በሰጠው ምላሽ፣ ወታደራዊ ልብስ ለብሰው በቤተ እምነቱ የተገኙ ሰዎች የሰሩት ወንጀል የለም ያለ ሲሆን፣ አለ ከተባለም በወታደራዊ ሕግ ሊጠየቁ ይችላሉ ሲል ተናግሯል።

እርሱ ይከሰሳል ስለመባሉ ሲመልስም “ነብይ እዩ ይከሰሳል የሚለው ደግሞ ለአንዳንድ ሰው የተለየ ሕግ ካለ ሊሆን ይችላል፤ የተለየ ሕግ ከሌለ ግን የሚያስከስስ አይደለም” ሲል ተናግሯል።

መከላከያ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫው “ጥቂት የሠራዊታችን አባላት ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ እንደነበሩ ተረጋግጧል” ብሏል።

የደንብ ልብሱን ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ አባላቱም በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸውን ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የማጣራት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝም አሳውቋል።

እዩ ጩፋ ለቀረበበት ክስ ምላሽ ሲሰጥ የመከላከያ አባላቱ የተሳተፉበት ፕሮግራም ከአንድ ወር በፊት ገደማ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሶ፤ የደንብ ልብስ የለበሱና የጦሩ አባል የሆኑ ወታደሮች ልክ እንደማንኛውም ሰው በአዲስ አበባ በሚገኘው ‘ክራይስት አርሚ ቤተ-ክርስቲያን’ ተገኝተው የዕለቱን ፕሮግራም መካፈላቸውን አስረድቷል።

አክሎም ማንኛውም በቤተ እምነቱ የሚገኝ ሰው ፕሮግራሙ እንደሚቀረጽና እንደሚተላለፍ እንደሚያውቅ ገልጿል።

“ልብሱን ለብሳችሁ ኑ አላልንም። እንደማንኛውም ምዕመን ለመታደም ነው የመጡት” በማለት ከዚህ ቀደምም የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንደሚመጡ እና እርሱ በሚመራው አገልግሎት እንደሚካፈሉ ባስተላለፈው የቪዲዮ መልዕክት ላይ ተናግሯል።

“እኛ ይሄ ሰው ይምጣ፤ ይሄኛው አይምጣ አንልም። እኛ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሁሉም ሰው ክፍት አድርጎ መጠበቅ ብቻ ነው” ብሏል።”

በእለቱ እኛ ጋር መጥተው ከአጋንንት እስራት ነጻ የሆኑ ሰዎች የሰሩት ወንጀል የለም። በወቅቱ የመጡት ወታደሮችም ልክ እንደ ማንኛውም አጋንንት ለቅቋቸው ሲሄድ ወድቀው ነበር። ይሄ ለሁሉም ሰው የሚሆን ነው። የተደበቀ ነገር አይደለም” ብሏል እዩ ጩፋ።

የቤተ-ክርስቲያኗ አገልግሎት በቴሌቪዥን እና በማህበራዊ ድረ-ገጾች ከዚህ ቀደምም እንደሚለቀቅ አስታውሶ፤ “ይሄም የተለየ ጉዳይ አይደለም” በማለት ተናግሯል።

“የመከላከያ ወታደሮች እንዲገኙ ኑ ብለን አልደወልንላቸውም። እኔ አገልግሎት የሰጠሁት የመከላከያ ካምፕ ሄጄ አይደለም። በቤተክርስቲያናችን ተገኝተው ነው የተገለገሉት። ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ለምን ተገኙ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው። የተገኙ ሰዎች ግን የሰሩት ወንጀል የለም”

‘ነብይ’ እዩ፤ “ብዙ አይነት ሰው ወደ እኛ ይመጣል” ካለ በኋላ፤ “እኛ ጋር ሲመጡ ግን አለባበሳችሁን አስተካክሉ አልያም ልብሳችሁን ቀይሩ የማለት ስልጣን የለንም። ቤተክርስትያን ለሁለም ናት፤ የሁሉም ናት” ሲል ተናግሯል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img