Sunday, September 22, 2024
spot_img

አና ጎሜዝ የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ ምርጫ ታዛቢ አልክም በማለቱ ማዘናቸውን ገለጹ – ኅብረቱ በትላንተናው እለት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ባደረገው ስብሰባ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ቃላት ተመላልሰዋል

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 26፣ 2013 ― የአውሮፓ ኅብረት በመጪው ወር ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ታዛቢዎችን እንደማይልክ ማሳወቁን ተከትሎ አና ጎሜዝ እጅግ በጣም ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

ኅብረቱ የምርጫ ታዛቢዎችን በተመለከተ እንደማይልክ ያሳወቀው ትላንት ምሽት ነበር፡፡ የአውሮፓ ኅብረት ታዛቢዎቹን ላለመላክ የወሰነው ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በሁኔታዎች ላይ መግባባት ስላልተደረሰ መሆኑን መሳወቁ መነገሩ የሚታወስ ነው፡፡

በውሳኔው እጅጉን ማዘናቸውን የገለጹት ፖርቹጋላዊቷ አና ጎሜዝ፣ በ1997 በተደረገው አገራዊ ምርጫ ወቅት የአውሮፓ ኅብረትን የምርጫ ታዛቢ ልኡክ የመሩ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ምርጫውን ተከትሎ ባወጡት ሪፖርት የወቅቱ መንግሥት ላይ በሰነዘሩት ነቀፌታ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ፖለቲካዊ እና ርእዮተ ዓለማዊ ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡

በሌላ በኩል የአውሮፓ ኅብረት የመረጃ አጣሪ ቡድን በትላንትናው እለት ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች ጋር በምርጫው ጉዳይ መወያየቱ ተነግሯል፡፡

በዚህ ውይይት ላይ ከኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ ከኢዜማ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንዲሁም የኦብነግ እና የባልደራስ ተወካይ መሳተፋቸው ሲነገር፣ አብን መቅረቱ ነው የተሰማው፡፡

በውይይቱ ላይ ሐሳባቸውን የሰነዘሩት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ነጻ እና ተአማኒ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችላት አቋም ላይ እንዳልሆነች ገልጸዋል የተባለ ሲሆን፣ በአንጻሩ የኢዜማው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ምርጫው ነጻ እና ተአማኒ ሊሆን እንደሚችል በመናገር ኅብረቱ ታዛቢዎችን እንዲልክ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡

በተጨማሪም በዚሁ ውይይት ላይ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናን ከጽንፈኛ ብሔርተኞች ጋር በማበር መክሰሳቸው ሲነገር፣ ፕሮፌሰር መረራ ለፕሮፌሰር ብርሃኑ በሰጡት መልስ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በናንተ ዓይነት መካሪዎች ተመርተው ነው ወደ ጥፋት እያመሩ ያሉት በማለት ሁሉንም ያሳተፈ ብሔራዊ መግባባት ሳይደረስ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት እንደማይቻል ተናግረዋል ነው የተባለው፡፡

በውይይቱ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሚመሩት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ከምርጫው ራሱን ማግለሉ ይታወቃል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img