Sunday, October 6, 2024
spot_img

የአውሮፓ ኅብረት በቀጣይ ወር የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ እንደማይታዘብ አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 26፣ 2013 ― ከሁለት ሳምንታት በፊት በውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ተወካዩ ጆሴፕ ቦሬል በኩል በግንቦት ወር የሚካሔደውን የኢትዮጵያን ምርጫ ለመታዘብ የምርጫ ታዛቢዎችን መላክ ወይም አለመላኬ የሚወሰው በአገሪቱ ቀጣይ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ ነው ብሎ የነበረው የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢዎቹን እንደማይልክ አስታውቋል፡፡

ኅብረቱ ታዛቢዎቹን እንደማይልክ በገለጸበት መግለጫው ምንም እንኳን የተቻለውን ሁሉ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በሁኔታዎች ላይ መግባባት ስላልተደረሰ ታዛቢ የመላኩ ነገር እንደተሰረዘ ነው ያመለከተው፡፡

በመግለጫው መጪው ወር መጨረሻ ለሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት ከ20 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሰው የአውሮፓ ኅብረት፣ ከምርጫ ጋር በተገናኘ እንዲሟሉልኝ ብጠይቅም ሊሟሉ አልቻሉም ያላቸውን ለታዛቢዎች ደኅንነት እና ገለልተኛነት ጠቃሚ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች ዘርዝሯል፡፡

የአውሮፓ ኅብረት በመጪው ወር ግንቦት 28 ይካሄዳል ተብሎ ቀጠሮ የተያዘለትን አገራዊ ምርጫ ለመታዘብ ልኡክ እንደማይልክ ማሳወቁን ተከትሎ ከመንግሥት በኩል እስካሁን ድረስ የተባለ ነገር ባይኖርም፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ዮናታን ተስፋዬ በትዊተር ገጻቸው ‹‹ልክ ላለፉት 20 ምናምን ዓመታት እንዳደረጉት አታላይና ጨካኝ አምባገነን ሁን፣ የውሸት ምርጫህን ለመታዘብ እግርህ ላይ ወድቀው ይለምኑሃል፤ ምንነታችሁን በደንብ እንድንረዳ ስላደረጋችሁ አመስግነናል›› ሲሉ የኅብረቱን ውሳኔ አጣጥለዋል፡፡ ጨምረውም ‹‹ኢትዮጵያ በፍፁም አትሸጥም፤ በመጨረሻ ግን ኢትዮጵያ ታሸንፋለች›› በማለት አክለዋል፡፡ ከቀናት በፊት 4 የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ም/ቤት አባላት በኢትዮጵያ ሊደረግ የታሰበው ምርጫ የሀገሪቱን ችግሮች አይፈታም ብለው ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወሳል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img