Sunday, October 6, 2024
spot_img

በቻድ አዲስ የሽግግር መንግሥት ተቋቋመ

አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሚያዝያ 25፣ 2013 ― በቀድሞ ፕሬዝዳንት ልጅ ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ የሚመራው የቻድ ጊዜያዊ ወታደራዊ ምክር ቤት ችግሮችን ለመፍታት በሚል የሽግግር መንግሥት መሰየሙን አስታወቀ፡፡

የሽግግር መንግስቱ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮችን ጨምሮ 40 ሚኒስትሮችንና ዴዔታዎችን ያካተተ ሲሆን፣ አዲስ የእርቅ ሚኒስቴር መቋቋሙም ተገልጿል፡፡

የፕሬዝዳንት ኤድሪስ ዴቢን ድንገተኛ ህልፈት ተከትሎ የተቋቋመውና በ14 ጄኔራሎች በተከበቡት መሐማት ኢድሪስ ዴቢ የሚመራው ወታደራዊ ምክር ቤት በ“ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት” የተመሰረተ ነው በሚል ይተቻል፡፡

ይሁን እንጂ የማርሻል ዴቢ ዋና ተፎካካሪ የሆኑት ሳሌህ ኬብዛቦ ለአዲሶቹ ባለሥልጣናት ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡

ሁለት የኬብዛቦ ፓርቲ ማለትም ብሔራዊ የዴሞክራሲና ሪፎርም ፓርቲ አባላትም ለእንስሳት እርባታ ሚኒስትርነት እና ምክትል ዋና ፀሐፊነት ተሹመዋል፡፡

ሌላኛው የኢድሪስ ዴቢ ኢትኖ ተቃዋሚ የሆኑት የ’ለነፃነት እና ልማት ፓርቲ’ው መሃማት አህማት አልሃቦ የፍትህ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውንም አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡

አብዛኛዎቹ የክልል ሚኒስትርነት የኃላፊነት ቦታዎች በሟቹ ፕሬዝዳንት የሀገር ማዳን ንቅናነቄ ፓርቲ እጅ ውስጥ እንደቀሩም ነው የጦሩ ቃል አቀባይ ጄኔራል አዜም በርማንዶአ አጎና በቴሌቭዝን በሰጡት መግለጫ ያስታወቁት፡፡

አብዛኞቹ የቀድሞ ሚኒስትሮች በነበሩበት እንዲቀጥሉ ካልሆነም በሌላ የኃላፊነት ቦታ እንዲሾሙ መደረጉንም ጀነራሉ ተናግረዋል፡፡

ለዚህም የቀድሞ የመንግሰት ቃል አቀባዩ ሸሪፍ መሃማት ዜኔ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲሁም የቀድሞ የመከላከያ ሚኒሰትር ዳውድ ያያ ብራሂም በነበሩበት እንዲቀጥሉ መደረጉንም በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በአዲሱ አዋጅ መሰረት የ37 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ማሃማት ኢድሪስ ዴቢ የ “እርቅ እና ውይይት ሚኒስቴር” የፈጠሩ ሲሆን በቅርቡም “ሁሉን አቀፍ ውይይት” ለማዘጋጀት ቃል ገብተዋል ፡፡በ18 ወራት ውስጥ “ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ” ለማካሄድም ነው ቃል ወታደራዊ ምክር ቤቱ የገባው፡፡

በሽግግር ቻርተሩ መሰረት ” የታጠቁ ኃይሎች የሚመራ ከፍተኛ ኮማንደር ” እንዲሁም ” ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እና ለብሄራዊ ደህንነት የሚዋቀረውን ኮሚቴ መሪ” መሰየምም ቀጣይ ስራዎች ናቸው፡፡

በምዕራቡ የሀገሪቱ ክፍል፤ ካኔም ግዛት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የተሰየመው የሽግግር መንግስት ከወታደር ቤቱ እና አማፅያን የተውጣጡ አካላት በውስጡ ያካተተ መሆኑን አል ዓይን ዘግቧል፡፡

ምክር ቤቱ ከፕሬዘዳንት ኤድሪስ ዴቢ ሞት በኋላ ተጥሎ የነበረውን የሰአት እላፊ ገደብ ማንሳቱ የሚታወስ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img