አምባ ዲጂታል፣ ሰኞ ሚያዝያ 25፣ 2013 ― የኢፌዲሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት በእዩ ጩፋ ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑን የሠራዊቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ አስታውቀዋል።
ለግለሰቡ ክስ ምክንያት የሆነው ‹‹በሃይማኖት ስም እየተከተሉኝ ነው ያላቸውን ግለሰቦች ክብር ባልጠበቀ መልኩ ከነዩኒፎርማቸው በቪዲዮና ፎቶ ቀርፆ በአደባባይ እንዲሠራጭ በማድረጉ›› መሆኑን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ዘግቧል፡፡
ይህ የሠራዊቱን ሥምና ታማኝነት በማሳጣት ለግል ፍላጎትና ጥቅም በማን አለብኝነትና ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን ፈጽሞታል ለተባለው ድርጊት ሠራዊቱ በሕግ ሊጠየይቀው መዘጋጀቱን ነው የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ያመለከቱት፡፡
ጥቂት የሰራዊታችን አባላትም ይህን ፍላጎት ለማሟላት የሁሉም ኢትዮጵያውያን መለያ የሆነውን ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ እንደነበሩ ተረጋግጧል ያሉት ኮሎኔሉ፤ ተሳታፊዎቹም በመከላከያ ወታደራዊ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ተይዘውና ታስረው ጉዳያቸውን ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የማጣራት ስራ እየተሠራ ይገኛል ተብሏል።
በዚህ አይነት ጥፋት ከዚህ ቀደም በተለያዩ የእምነት ተቋማት የተገኙ አባላት ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዶ እንደነበረ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፣ ወደፊትም ማንኛውም የሠራዊት አባል የየትኛውም እምነት ተከታይ ቢሆን በእንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ ተሳትፎ ከተገኘ ተጠያቂ ይሆናል ብለዋል፡፡
የእምነት ተቋማትና መላው ሕዝብ የመከላከያ ሠራዊቱን ዩኒፎርሙን ለብሶ በእምነት ተቋማት፣ በሕዝቡ ዘንድ ነውር በተባሉ የመጠጥ፣ የሱስ፣ የቁማርና ተመሳሳይ ቦታዎች የሰራዊት አባልም ሆነ ተመሳሳይ ዩኒፎርም ለባሽ ሲመለከት እንዲጠቁም ጥሪ አቅርበዋል።
አሁን በሠራዊቱ ክስ ሊመሠረትበት መሆኑ የተነገረው እዩ ጩፋ፣ ክራይስት አርሚ ኢንተርናሽናል የተሰኘ የፕሮቴስታንት ቤተክርስትያን መስርቶ በርካታ ተከታዮችን ማፍራቱ የሚነገርለት ሲሆን፣ ራሱን ‹‹ነብይ እና ሐዋርያ›› በማለት የሚጠራ ነው፡፡