Sunday, September 22, 2024
spot_img

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ ሊነሳ እንደሚችል ሱዳን አስጠነቀቀች

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 23፣ 2013 ― በታላቁ የህዳሴ ግድብ ድርድሮች እና ሁለቱ አገሮች በይገባኛል በሚወዛገቡባቸው የድንበር ጉዳዮች የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የሚያቀርቧቸው መከራከሪያዎች መልሰው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የሉዓላዊነት ጥያቄ እንደሚያስነሱ ሱዳን አስጠነቅቃለች፡፡

የሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ትላንት አርብ ዕኩለ ለሊት ገደማ ባወጣው መግለጫ፤ የሁለቱ አገሮች ልዩነት በግድቡም ሆነ በድንበር ውዝግባቸው መበርታቱን የሚጠቁም የከረረ ትችት በኢትዮጵያ ላይ ሰንዝሯል።

የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በትላንት መግለጫው፣ ሱዳን ኢትዮጵያን በአባይ ውሃ እና በድንበር ጉዳዮች ላይ ከተፈረሙ የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ለማቆራኘት እየሰራች ነው እያሉ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ የሚሰጧቸውን መግለጫዎች በጥልቅ ሀዘኔታ እየተከታተለ መሆኑን ገልጿል።

‹‹አገራት እና መንግሥታት በቀደሙ አገዛዞች እና መንግሥታት ለተፈረሙ ስምምነቶች እና ውሎች ቁርጠኛ መሆናቸው በዓለም አቀፍ ግንኙነት መሠረት የጣለ ልማድ ነው›› ያለው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ፣ ‹‹ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እና ውሎችን፤ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን በማውጣት፣ ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል እነርሱን የሚቃረን የህዝብ አስተያየት በማደራጀት ገሸሽ ማድረግ፤ ዓለም አቀፍ ግንኙነትን የሚበክል፣ ለአንድ ወገን ፍላጎት ተጋላጭ የሚያደርግ፣ ቀውስን የሚያስፋፋ፣ የጥሩ ጉርብትና መሠረትን የሚያናጋ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር›› እንደሆነ በመግለጽም የከረረ ተቃውሞ ሰንዝሯል።

የሱዳን ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በመግለጫው ‹‹አሳሳች ሀሳብ ማቅረብ እና ከዚህ ቀደም የተፈረሙ ስምምነቶችን ውድቅ ማድረግ ማለት ከስምምነቶቹ በአንዱ ከሱዳን ተላልፎ በተሰጠው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ሉዓላዊነት ጥያቄ ውስጥ መክተት እንደሆነ ለኢትዮጵያ ማስታወስ አያስፈልገንም›› የሚል ማስጠንቀቂያ መስጠቱንም የኢትዮጵያ ኢንሳይደር ዘገባ አመልክቷል፡፡

በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል በተለይ በሁለቱ አበይት ጉዳዮች ምክንያት የበረታው ውጥረት የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካንን ጨምሮ ዓለም አቀፉን የዲፕሎማሲ ማህበረሰብ ካሳሰቡ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን የሾሟቸው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ በአፋጣኝ መፍትሔ ከሚያፈላልጉላቸው ቀውሶች መካከል የኢትዮጵያ እና ሱዳን ግንኙነትን ያሻከሩት ሁለቱ ጉዳዮች በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img