Sunday, October 6, 2024
spot_img

አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች መጪው ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ባሰ ችግር እንዳያስገባት ስጋት እንዳላቸው ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 23፣ 2013 ― አምስቱ የአሜሪካ ሴናተሮች ማለትም ቤን ካርዲን፣ ቲም ካይን፣ ጃክ ሮዘን፣ ኮሪ ቡከር እና ኤድ ማርኬይ ይህን ስጋታቸውን የገለጹት አገራቸው አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ አሳሳቢ ላለቻቸው ወቅታዊ ችግሮች መፍትሔ የማፈላለግ ኃላፊነት ለጣለችባቸው አዲሱ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በጻፉት ደብዳቤ ነው፡፡

ሴናተሮቹ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ አለ ያሉት ችግር እጅጉን እያሳሰባቸው እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን፣ በተለይ በትግራይ ክልል ካለው ግጭት ጋር በተገናኘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዐሕመድ የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ሁሉንም ዓይነት ዲፕሊማሲያዊ መንገዶች እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል፡፡

ሴናተሮቹ በትግራይ ክልል እንዲፈጸም የሚፈልጉት የኤርትራ ወታደሮች እንዲወጡ፣ ያልተገደበ የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ እና የደረሰው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በገለልተኛ አካል ተጣርቶ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ መሆኑን ዘርዝረዋል፡፡

ከትግራይ ክልል በተጨማሪም በኦሮሚያ፣ በአማራ እና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ደርሷል ያሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ማጣራት እንዲደረግበት አመልክተዋል፡፡

አዲሱ የአሜሪካ መንግሥት ሹመኛ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ በሳምንቱ መጀመሪያ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ አንቶንዮ ብሊንክን ማሳወቃቸው አይዘነጋም፡፡

አዲሱ አምባሳደር ጄፍሪ ፌልትማን በቅርቡ በኢትዮጵያ መሬት ላይ የሚገኙ የኤርትራ ወታደሮችን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር መነጋጋር እንደሚፈልጉ ለፎሬን ፖለሲ መጽሔት ነግረውት ነበር፡፡

በአደባባይ ዲስኩሮች ወታደሮቹ የኢትዮጵያን መሬት ለቀው እንደሚወጡ ቢነገርም፣ መሬት ላይ ያለው ሐቅ ግን እሱን እንደማያመለክት የጠቆሙት አዲሱ ሹመኛ፣ እንዲያውም የኤርትራ ወታደሮች እየተጠናከሩ እንደሚገኙ በመናገር ብስጭታቸውንም ገልጸዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img