አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሚያዝያ 21፣ 2013 ― የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ገዢው ፓርቲ ‹‹ሁሉን አቀፍ ያልሆነ›› ነው ያለውን መጪውን ምርጫ ማካሄዱን አቁሞ ‹‹የዕርቅና ብሔራዊ መግባባት መድረክ እንዲያመቻችና አገራችን ከተጋረጠባት መመሰቃቀል እንዲድትወጣ›› እንዲደርግ ሲል በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡
ፓርቲው በመግለጫው መላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሀገሪቱ ዴሞክራሲ ኃይሎችና የዓለም ማኅበረሰብም ‹‹ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ እንድወጣ የየበኩላችሁን አስተዋጽኦ እንዲታደርጉ›› በማለትም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
‹‹ዛሬ ሀገራችን በቀውስ እየተናጠች ነው›› ያለው ፓርቲው፣ የአገሪቱ አንዳንድ ክፍሎች በኮማንድ ፖስት ሥር እንደሚተዳደሩ በመጠቆም የሕግ የበላይነት እየተከበረ እንዳልሆነም ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ኦፌኮ የአገሪቱ ዋና ከተማና አንዳንድ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ አገልግሎችን ‹‹አንድም ጨርሶ አያገኙም፤ ወይም በበቂ ሁኔታ አያገኙም ወይም ሊከፍሉት ከሚችሉት ዋጋ በላይ ይጠየቃሉ›› ያለ ሲሆን፣ ‹‹ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ሕወሓት/ኢህአዴግ በመቀጠልም የብልፅግና ፓርቲ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ ሲያደርሱ ከቆዩት የመልካም አስተዳደር ጉደለት የተነሳ መሆኑ በማንም የማይታበል ሐቅ ነው›› ሲል አስፍሯል፡፡
አገሪቱ ገብታበታለች ያለው ውስብስብ ችግር በብሔራዊ መግባባት እንዲፈታ ሲወተውት መቆየቱን ያስታወሰው ፓርቲው፣ ‹‹ከነዚህ አስከፊ ችግሮች ለመላቀቅ መፍትኼ መሻት ይኼን ያህል ቀላል ይሆናል ተብሎ ባይገመትም፣ መንግሥት ከብሔራዊ መግባባት መሸሹ ሕዝባችንን ለበለጠ አደጋ ከማጋለጥ የበለጠ ፋይዳ›› ያለው ነገር አይደለም ሲል አሳስቧል፡፡