አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሚያዝያ 20፣ 2013 ― በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የተቀመጠውን መስፈርት አላሟሉም ተብለው ፍቃዳቸው ከተሰረዙ ፓርቲዎች መካከል አንዱ የሆነው የገዳ ፓርቲ መጪው ብሔራዊ ምርጫ በስድስት ወር እንዲራዘም መጠየቁ ተሰምቷል፡፡
ይህንኑ ጉዳይ በሚመለከት ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ ጥያቄውን ማቅረቡን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሮበሌ ታደሰ ለሚዲያዎች ገልጸዋል፡፡
‹‹በምርጫ ቦርድ ምክንያት ከምርጫ ውጪ ሆነናል›› ያሉት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሮበሌ፣ መጪው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በስድስት ወር ተራዝሞ መስከረም 2014 እንዲካሄድ ለቦርዱ ጥያቄ ማቅረባቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
ሆኖም በቀጣዩ ወር አገራዊ ምርጫውን ለማካሄድ ሽርጉድ እያደረገ የሚገኘው ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ያለው ነገር የለም፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ደንብ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና ሥነ ሥርዓት ቁጥር 1162/2011 መሰረት በማድረግ በአገሪቱ በምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአዋጁ በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ድጋሚ ምዝገባ እንዲያከናውኑ መደረጉ ይታወሳል።
ቦርዱም በአዋጁ የተቀመጠውን መስፈርት አላሟሉም በማለት በግንቦት ወር 2012 መሰረዛቸውን ካስታወቃቸው ፓርቲዎች መካከል የገዳ ሥርዓት ፓርቲ አንዱ ነበር።
ነገር ግን የገዳ ሥርዓት ለኦሮሞ ነጻነት ፓርቲ ጉዳዩን ፍርድ ቤት ወስዶት በነበረው ክርክር ፍቃዱ መሰረዙ ትክክል እንዳልሆነ እንደተወሰነለት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሮበሌ ታደሰ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል በፌዴሬሽን ሥርዓት ኢትዮጵያ ደግሞ በኮንፌዴሬሽን መዋቀር አለባት የሚል ፕሮግራም እንዳከለው የሚናገረው የገዳ ሥርዓት ፓርቲ፣ በ1995 የተመሰረተ ሲሆን፣ ባለፉት ሦስት አገራዊ ምርጫዎች መሳተፉም ተነግሯል፡፡