አምባ ዲጂታል፣ ረቡዕ ሚያዝያ 20፣ 2013 ― የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በኢትዮጵያ በርትቷል ያለውን አፈና እና ግድያ በተመለከተ በጥር ወር ለአፍሪካ ኅብረት፣ ለአውሮፓ ኅብረት፣ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት እና ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ‹‹ከሕገ መንግሥታዊ ቀውስ እና ብጥብጥ ለመታደግ ጥብቅ እርምጃ እንዲወስዱ›› ያስገባሁት አቤቱታ በድጋሚ እንዲታይ ሲል በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡
ድርጅቱ በመግለጫው በአሁኑ ወቅት ‹‹የአገሪቱ የደህንነት ሀኔታ እና የፓለቲካ አለመረጋጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሆኑ እጅግ አሳስቦናል›› ያለ ሲሆን፣ ‹‹ሁኔታዎች መገመት በማይቻልበት ፍጥነት እየተባባሱ ለከፍተኛ ሥርዓት አልበኝነት መንገሥ በር ከፍቷል›› ሲል አስፍሯል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያሳተፈ ሁለንተናዊ የፖለቲካ ወይይት ካልተካሔደ፣ መሪዎቻቸውን ጨምሮ የፖሌቲካ እስረኞች ካልተፈቱ፣ አወዛጋቢውና ወዳቂ የሆነውን የምርጫ ሂደት በድጋሚ እንዲታይ ካልተደረገ፣ በሀገሪቱ የነገሰው ጽንፈኝነት እና ውጥረት በመባባስ ወደ ለየለት ሥርዓት አልበኝነት እና ደም መቃባት ሊያመራ ይችላል›› ሲልም ጨምሮ አሳስቧል፡፡
አሁን ያሉ ችግሮችን ለማቃለል የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ‹‹እያከናወነ ነው›› ያለውን ተግባር ያመሰገነው ኦነግ፣ ‹‹ከጉዳዩ አሳሳቢነት የተነሳ አሁንም ተጨማሪ ስራ እንደሚጠበቅባችሁ እና ችግሮቹ ሁለንተናዊ መፍትሔ አስክያገኙ ጭምር የበኩላችሁን ድርሻ እንድትወጡ›› በማለት አስገንዝቧል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በመጪው ወር ከሚካሄደው አገራዊ ምርጫ ራሳቸውን ካገለሉ ሁለት ፓርቲዎች መካከል አንደኛው መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡