አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 10፣ 2014 ― የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (የተመድ) በኢትዮጵያ ታስረውብኛል ካላቸው 16 ሠራተኞች መካከል አምስት ሲቀሩ መለቀቃቸውን በቃል አቀባዩ ስቴፋን ዱያሪክ በኩል አስታውቋል፡፡
ዱያሪክ ይህን የተናገሩት በትላንትናው እለት በሰጡት መግለጫቸው ነው፡፡
ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ በቁጥጥር ስር ውለዋል ከተባሉ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የርዳታ መኪና አሽከርካሪዎች መካከል ግማሾቹ መለቀቃቸውን ድርጅቱ አስታውቆ ነበር፡፡
ታስረዋል የተባሉት የዓለም ምግብ ፕሮግራም 72 የከባድ መኪና አሸከርካሪዎች ሲሆኑ፣ በአፋር ክልል ሰመራ ውስጥ በቁጥጥር ስር እንደዋሉ የተለያዩ የዜና ምንጮች አመልክተው ነበር፡፡
አሁን መለቀቃቸው የተነገረውን እንዲሁም በቁጥጥር ስር የሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሠራተኞችን በተመለከተ ለምን እንደታሰሩ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የተመድ አሊያም የሌላ ተቋም ሰራተኛ በመሆኑ የታሰረ ግለሰብ አለመኖሩን አስታውቀው ነበር፡፡
ቃል አቀባዩ፣ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የሚንቀሳቀስ የትኛውም ተቋም ሰራተኛ የሀገሪቱን ሕግ አክብሮና ጠብቆ ሊሰራ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ሰኞ፣ ኅዳር 6፣ 2014 በኒውዮርክ መግለጫ የሰጡት የተመድ ዋና ጸሐፊ ቃል ፈርሃን ሃቅ የድርጅቱ አሽከርካሪዎች መካከል 34ቱ አሽከርካሪዎች ቢፈቱም፣ ሌሎች 36 በእስር ላይ እንደሚገኙ አስረድተው ነበር፡፡