Saturday, November 23, 2024
spot_img

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ በምርጫው ምክንያት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀሩ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሰኔ 10፣ 2013 ― እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ዛሬ ለነበራቸው ቀጠሮ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት ጉዳያቸውን ለመከታተል ችሎት ሳይቀርቡ መቅረታቸው ተሰምቷል፡፡

ጉዳያቸውን የሚመለከተው ፍርድ ቤት እንዳለው ‹‹ለተከሳሾች እና ለሰፊው ማኅበረሰብ ደኅንነት ሲባል ተከሳሾች ችሎት ፊት መቅረብ አይችሉም›› ሲል ትዕዛዝ መስጠቱን የቢቢሲ ዘገባ ያመለክታል፡፡

በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር የተዘረዘሩ ተከሳሾች ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀጠሮ ነበራቸው።

የእነ አቶ ጃዋር መሐመድን ጉዳይ እየተመለከቱ ያሉት ዳኞች ባለፉት ጥቂት ቀናት ከፍተኛ የሆነ የምርጫ ቅስቀሳ ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።

‹‹ለተከሳሾች ከፍተኛ ጥበቃ ነው የሚያስፈልገው›› በማለት በምርጫ ወቅት ተከሳሾችን ወደ ችሎት ማምጣቱ አስቸጋሪ ነው በማለቱ፣ ፍርድ ቤቱ አቶ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ 24ቱ ተከሳሾች ከምርጫው በኋላ ፍርድ ቤት ይቅረቡ ሲል ወስኗል።

ዐቃቤ ሕግ ችሎቱ በዝግ ይከናወን እንዲሁም ምስክሮቼ ከመጋረጃ ጀርባ ቃላቸውን ይስጡ በሚል አሻሽሎ ባቀረበው አቤቱታ ላይ ተከሳሾች ምላሽ እንዲሰጡ ነበር የዛሬው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ ችሎት 1ኛ የፀረ ሸብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ቀጠሮ ተይዞ የነበረው።

በዛሬ ችሎት ምንም እንኳ በችሎቱ ተከሳሾቹ ባይገኙም ሦስት የተከሳሽ ጠበቆች ተገኝተዋል። ጠበቆቹም ዐቃቤ ሕግ አሻሽሎ ላቀረበው አቤቱታ ‹‹ያዘጋጀነው ምላሽ በተከሳሾች እጅ ስለሚገኝ የምንሰጠው ምላሽ የለም›› ብለዋል።

ፍርድ ቤቱም በአቶ ጃዋር መዝገብ ሥር የተከሰሱ ተከሳሾችን ጉዳይ ለመመልከት ለሰኔ 21፣ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ አባልና አመራር የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ከ20 በላይ ተከሳሾች ጉዳያቸውን ፍርድ ቤት ቀርበው እንደማይከታተሉ ግንቦት 18፣ 2013 በዋለው ችሎት ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img