አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ ጥር 17፣ 2016 – የራስ ገዟ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ሙሴ ቢሂ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረምነው የመግባቢያ ስምምነት የባሕር ኃይል ጣቢያ ስለማቋቋም እንጂ አዲስ የወደብ አገልግሎትን አይመለከትም ያሉት በሚመሯት ሶማሊላነድ ብሔራዊ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ነው፡፡
ሙሴ በዚህ ቆይታ በስምምነቱ መሠረት ኢትዮጵያ የምትወስደውን ጠረፍ ለወታደራዊ ዓላማ ብቻ እንደምትጠቀምበት በአጽንኦት በመግለጽ፤ ሸቀጦችን ለማጓጓዝ ተግባር አይውልም ብለዋል፡፡ በአዲሱ ስምምነት ሸቀጦች እንደማይጓጓዙ የገለጹት ቢሂ፤ ኢትዮጵያ ለወጪና ገቢ ንግዷ ሌላኛውን ወደብ በርበራን ብቻ እንደምትጠቀም ጠቁመዋል።
ከአንድ ወር በፊት አዲስ አበባ ተገኝተው ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የተፈራረሙት የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት፤ በወቅቱ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ሶማሊላንድ ለኢትዮጵያ የባሕር ጠረፍ በመስጠት በምትኩ የአገርነት እውቅና እንደምታገኝ ተናግረው ነበር፡፡ ይኸው የቢሂ ንግግር ሶማሊላንድ አሁንም ድረስ የግዛቴ አካል ናት በምትለው ሶማሊያ በኩል ተቃውሞ አስነስቷል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ቢሂ ከሶማሊላንድ ብሔራዊ ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታም ይህንኑ ጉዳይ አንስተዋል፡፡ የመጨረሻው ስምምነት አለመፈረሙን ያስታወሱት ሙሳ ቤሂ፤ ይኸው ስምምነት ሲፈረም ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ የአገርነት እውቅና መስጠቷ ይፋ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ባደረጉት የመግባቢያ ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ የባህር ጠረፍ ስታገኝ ትሰጣለች ከተባለው የአገርነት እውቅና በተጨማሪ፤ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ድርሻ እንደምትሰጥ በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተነግሯል፡፡ ሶማሊላንድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የምትወስደው ድርሻ ምን ያህል ነው የሚለውን በተመለከተ ግን የተገለጸ ነገር የለም፡፡