የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ ያሳሰበው ዛሬ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ ነው።
ኮሚሽኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችንና አባላትን፣ የሚዲያ አባላትንና የማኅበረሰብ አንቂዎችን ዒላማ ያደረገ እስር እና ወከባ በእጅጉ አሳሳቢ መሆኑን በመግለጽ፣ በተለያየ ዓይነት ወንጀል ተጠርጥረው በፖሊስ ከተያዙ ሰዎች ውስጥ በተለይ የሚዲያ አባላትን፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላትን እንዲሁም የማኅበረሰብ አንቂዎችን ጉዳይ በተመለከተ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ገልጿል።
ከእነሱም መካከል ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ በቁጥጥር ስር የዋሉ፣ የሚዲያ አዋጁን በሚጻረር መልኩ የታሰሩ፣ በተራዘመ ቅድመ-ክስ እስር ወይም ክስ ሳይመሠረትባቸው በእስር የቆዩ መኖራቸውን፣ በተወሰኑት ላይ የወንጀል ክስ ተመሥርቶ የነበረ ቢሆንም ክሱ በበቂ ማስረጃ የተደገፈ ባለመሆኑ በፍርድ ቤት ውሳኔ ውድቅ ተደርጎ ወይም በፖሊስ ውሳኔ ከተራዘመ እስር በኋላ በነጻ ወይም በዋስትና የተለቀቁ መኖራቸውንም ኮሚሽኑ ተመልክቻለሁ ብሏል።
በዚህ ወር ውስጥ ብቻ ከታሰሩ የሚዲያ አባላት መካከል የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር የሥራ አስፈጻሚ አባል የሆነው ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻውን (አራት ኪሎ ሚዲያ) ጨምሮ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው (የኔታ/መድሎት ሚዲያ)፣ ጋዜጠኛ አራጋው ሲሳይ (ሮሃ ኒውስ)፣ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስፋው (ኢትዮ ሰላም)፣ ጋዜጠኛ ጌትነት አሻግሬ (የአማራ ድምፅ)፣ ጋዜጠኛ በየነ ወልዴ (ጉራጌ ሚዲያ ኔትወርክ )፣ ጋዜጠኛ ሰናይት አያሌው (አሻራ ሚዲያ) ጋዜጠኛ ሳሙኤል አሰፋ (ኢ ኤም ኤስ) እንዲሁም በማኅበረሰብ አንቂነት እና በሚዲያ ሥራም የሚታወቁት መስከረም አበራ (ኢትዮ ንቃት) እንገሚገኙበት ዘርዝሯል።
ከፊሎች በእስር ወቅት ተገቢ ላልሆነ አያያዝ የተዳረጉ፣ ከፊሎች ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ እስር ተዳርገው የነበሩ እና፣ ከፊሎችም ከተለያየ ጊዜ መጠን እስር በኋላ የተለቀቁ መሆናቸውንም ጠቅሷል።
መንግሥት የወንጀል ተግባሮችን ሁሉ የመከላከል፣ የመመርመርና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና የማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚያተኩር እስር ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመደራጀትና በሕዝባዊ ጉዳዮች የመሳተፍ መብቶች ላይ የሚያስፈራራ፣ የሚያሸማቅቅ እና የሚገድብ ውጤት እንዳይኖረው ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚሻ መሆቱን ያመለከተው ኮሚሽኑ፣ በመሆኑም የመንግሥት የጸጥታ አካላት በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና በማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ካተኮረ እስርና ማዋከብ እንዲቆጠቡ፣ በወንጀል የተጠረጠሩና በበቂ ሕጋዊ ምክንያት በቅድመ-ክስ ሊታሰሩ የሚገባቸው ሰዎች በሚኖሩበት ሁኔታም በሕግ በተመለከተው መንገድ ብቻ በጥብቅ ጥንቃቄ አንዲፈጸምና የተጠረጠሩ ሰዎችን ሁሉ ከምርመራ በፊት ከማሰር እንዲቆጠቡ፣ በተጨማሪም በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ መሠረት በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት በመፈጸም የተጠረጠረ ማንኛውም ሰው ወይም አካል፣ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ለተጨማሪ ምርመራ በእስር እንዲቆይ ሳይደረግ ክሱ በቀጥታ በዐቃቤ-ሕግ አማካኝነት ለፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት መሆኑ በግልጽ የተደነገገ በመሆኑ፤ በዚሁ መሠረት እንዲፈጸምና በሚዲያ አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ተጠርጣሪ የሆኑ ታሳሪዎች በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ አሳስቧል።