Saturday, November 23, 2024
spot_img

የወልቃይት ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚመራው ሥርዐት መሠረት እንደሚፈታ መንግሥት አስታወቀ

አምባ ዲጂታል፤ እሑድ ታኅሣሥ 23፣ 2015 ― በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የሚገኘውን የወልቃይት አካባቢ የወሰን ማካለል ጉዳይ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚዘረጋው ሥርዓት መሠረት እንደሚፈታ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ሬድዋን ሑሴን ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የፌዴራል መንግሥትና ሕወሓት ሲካሄድ ከነበረው የሁለት ዓመታት ውጊያ ወጥተው የጀመሩትን የሰላም ስምምነት አስመልክቶ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ እንዳስነበበው ከ50 በላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተሳተፉበት በዚህ የውይይት መድረክ በርካታ ፖለቲከኞች አከራካሪ ስለሆነው ስለወልቃይት ባለቤትነት፣ ስለኤርትራ ወታደሮች፣ ስለሰላም ስምምነቱ ግልጽነትና የመረጃ አሰጣጥ፣ እንዲሁም ስለ ሰላም ስምምነቱ ተደራዳሪዎች በርካታ ጥያቄዎች አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራሲ ፓርቲ (የኢሶዴፓ) ምክትል ፕሬዚዳንት ራሔል ባፌ (ዶ/ር) ከወልቃይት ጋር እየተነሳ ያለው ጉዳይ፣ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ በአንድ በኩል የባህር በር ስታጣ በሌላ በኩል ደግሞ ወልቃይትን በመቀማት አገሪቱ ከሌላ አገር ጋር እንዳትገናኝ ለመዝጋት የተደረገ እንቅስቃሴ በመሆኑ መንግሥት ጉዳዩን እንዴት እየተከታተለው ነው ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ የወልቃይት ጉዳይ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታል ብለዋል፡፡ ከጅምሩ የጦርነቱ ዓላማ ወልቃይትን ማስመለስና ሕወሓትን ማጥፋት አልነበረም ያሉት ሬድዋን፣ የጦርነቱ ዋና ዓላማ የነበረው የአገሪቱን ሉዓላዊነት ማስከበርና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ማስፈን የሚሉት እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡‹‹ሕወሓትን እንደ ፖለቲካ ኃይል የማጥፋት ዓላማ ያለው ሰው ይኖራል፣ ነገር ግን የፌዴራል መንግሥቱ ዓላማ አይደለም›› ብለዋል፡፡ ‹‹ወልቃይት በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል ያለ ፀብ ነው፣ በሁለት ክልሎች መካከል ያለው ፀብ ደግሞ የሚፈታው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሚመራው ሥርዓት፤›› ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹የፌዴራል መንግሥት አቋም ተራ በተራ ጡንቻ እየተፈታተን አንዳችን ሌላችንን ማንበርከክ ይቁም›› የሚል መሆኑን የገለጹት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው፣ ‹‹ወልቃይትን ከዚህ ቀደም ሕወሓት ጡንቻ ስለነበረው በጉልበት ወስዷል፣ አሁን ደግሞ ሕወሓት ሸብረክ ሲል ጡንቻ ያለው አካል ይውሰድ ካልን መጪው ትውልድ 20 ዓመት ጠብቆ ድንገት ጡንቻ ካገኘ ይወስደዋል፡፡ ስለዚህ ዘላቂው መፍትሔ ጡንቻ ሳይሆን ሕግና ሥርዓት ነው›› በማለት ገልጸዋል፡፡

‹‹አንድ ሰው ትግራይን ሲወድ ካርታውን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡን ነው፣ ነገር ግን ካርታውን ወዶ ሕዝቡን መጥላት አይቻልም›› ሲሉም አክለዋል፡፡ ‹‹ቲፎዞና ደም መርጠን መለቃቀስ ይቅር፣ የትም ቦታ ሰው ሲሞት ሁላችንም  ሊሰማን ይገባል›› ብለዋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img