አምባ ዲጂታል፤ ቅዳሜ ሐምሌ 23፣ 2014 ― ከሰሞኑ አዲስ አበባ ከተገኙት አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር ጋር የተወያዩት የኦሮሞ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመናብርቱ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና እና አቶ ዳውድ ኢብሳ ናቸው፡፡
ሁለቱ መሪዎች ከልዩ መልዕክተኛው ጋር ያካሄዱትን ውይይት በተመለከተ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለአምባ ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር መረራ እርሳቸው እና ዳውድ ኢብሳ ከአሜሪካው ልዩ መልእክተኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ በኢትዮጵያ ስለሚደረግ ሁሉን አቀፍ ውይይት፣ የሰሜኑ ጦርነት አደራዳሪዎች ሁኔታ፣ ስለ አገራዊ ለውጡ አሁናዊ ሁኔታ፣ የኦሮሚያ ክልል ወቅታዊ ጉዳይ እና ሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡
ከእነዚህ መካከል ሃያ ወራት ያስቆጠረውን የሰሜኑን ጦርነት ለመቋጨት በሚደረገው የሰላም ንግግር አደራዳሪዎችን በተመለከተ፤ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ብቻ የሚለው አዋጭ እንዳልሆነ መግለጻቸውን አመልክተዋል፡፡ ለዚህ ምክንያት አድርገው የጠቀሱት ኅብረቱ በአፍሪካም ሆነ በሌላ አህጉር በተመሳሳይ ሁኔታዎች ላይ ልምድ የሌለው መሆኑን ነው፡፡ በዚህም አፍሪካ ህብረት በተናጠል የኢትዮጵያን ጉዳይ ለብቻው ማደራደር እንደሌለበትና ከዚያ ይልቅ ሌሎችም ማለትም የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ ጭምር ተካተው አደራዳሪነቱ በጋራ እንዲሆን እርሳቸውም ሆነ አቶ ዳውድ ሐሳብ መስጠታቸውን ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት በሚደረገው ድርድር ተደራዳሪዎቹን ይፋ ያደረገው የፌዴራል መንግስት ድርድሩ በአፍሪካ ኅብረት ማዕቀፍ ውስጥ መካሄድ እንዳለበት በተደጋጋሚ የገለጸ ሲሆን፣ ሌላኛው ተደራዳሪ ሕወሓት በበኩሉ በአፍሪካ ህብረት ላይ ያለውን ጥርጣሬ በመግለጽ ለአደራዳሪነት የኬንያውን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን መምረጡ መነገሩ ይታወሳል፡፡
የኦፌኮ ሊቀመንበር በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር በተመለከተም አሁን ምእራባዊያን የሚያተኩሩት ሰሜኑ ክፍል ላይ መሆኑን በማንሳት፤ ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ችግር ጠቅሰው እኩል ትኩረት እንዲሰጡ ማስገንዘብም የውይይታቸው አካል እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በተገናኘ አገራዊ ለውጡ ቀውስ ወለድ እና በጣም በርካታ ችግሮችን ያስከተለ መሆኑን ያመለከቱት ፕሮፌሰር መረራ፤ ለዚህ ችግር ዋንኛው መፍትሔ ሁሉን አቀፍ ውይይት እና ድርድር መሆኑን በመግለጽ እገዛ እንደሚያስፈልግ መናገራቸውን አስረድተዋል፡፡
የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር መወያየታቸው መነገሩ አይዘነጋም፡፡ ልዩ መልእክተኛው በዚህ ዙር ጉዟቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች እና ግብጽ መዳረሻቸው ነው፡፡