Saturday, November 23, 2024
spot_img

ሲያወዛግቡ የቆዩት የጎረቤት ሶማሊያ ወታደሮች ሥልጠና ማጠናቀቃቸውን የኤርትራ መንግሥት ገለጸ

  • የሶማሊያ ወታደሮች በሰሜን ጦርነት ከፌዴራል መንግሥት ጎን ተሰልፈው ተሳትፈዋል የሚሉ መረጃዎች ወጥቶ ነበር

አምባ ዲጂታል፤ ሰኞ ሐምሌ 4፣ 2014 ― የኤርትራ መንግስት ላለፉት ሁለት ዓመታት በሶማሊያ አወዛጋቢ ሆነው የቆዩት እና በአገሪቱ የሚገኙ የሶማሊያ ወታደሮች ወታደራዊ ስልጠናቸውን አጠናቅቀው ተመርቀዋል ሲል ያስታወቀው ትላንት ሐምሌ 3፣ 2014 ነው፡፡

የወታደሮቹ የመመረቅ ዜና የመጣው አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝደንት ሐሰን ሸይኽ ማሕሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብንት ወደ አስመራ ካቀኑ በኋላ ነው፡፡ ይህንኑ ተከትሎ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የወታደሮች የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ መገኘታቸውን የሚያሳዩ ምስሎች እንዲሁም ዘገባዎች ተጋርተዋል፡፡

መረጃውን ያጋሩት የኤርትራ ኢንፎርሜሽን ሚንስትር የማነ ገ/መስቀል በትዊተር ገጻቸው ከተመራቂዎቹ የሶማሊያ ወታደሮች መካከል ለሦስት ዓመታት ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

የማስታወቂያ ሚኒስትሩ የማነ ገብረመስቀል ኤርትራ ያሉ የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር አባላት በፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና በሐሰን ሼክ ማሕሙድ ሲጎበኙ የሚያሳይ ፎቶ በገጻቸው ይፋ ያደረጉ ቢሆንም፤ምን ያክል የሶማሊያ ወታደሮች ስልጠናቸውን እንዳጠናቀቁም የሥልጠናውን ዐይነት በተመለከተ የሰጡት መረጃ የለም፡፡  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እና የሕወሓት ኃይሎች ከዚህ ቀደም የሶማሊያ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ከፌደራል መንግሥቱ ጎን ተሰልፈው እየተዋጉ ነው ብለው ነበር፡፡

የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ከአንድ ዓመት በፊት ባወጣው ሪፖርት በኤርትራ የሰለጠኑ የሶማሊያ ወታደሮች ከፌደራሉ መንግሥት ጎን በመሰለፍ በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል ብሏል።

ሶማሊያውያን ወታደሮች በትግራይ ጦርነት ተሳትፈዋል የሚል ሪፖርት በስፋት መውጣቱን ተከትሎ ሶማሊያውያን ወላጆች ልጆቻችንን አምጡ በሚል በአገሪቱ መዲና ሞቃዲሾ እና በሌሎች ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ማካሄዳቸው በስፋት ተዘግቦ ነበር።

እንደ ሪፖርቶች ከሆነ የሶማያ ወታደሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኤርትራ የተላኩት በፈረንጆቹ 2019 ላይ ሲሆን፣ ወታደሮቹ ሶማሊያን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ኳታር ለምታዘጋጀው የዓለም ዋንጫ በጥበቃነት እንደሚሰሩ ተነግሯቸው ነበር ተብሏል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img