Saturday, November 23, 2024
spot_img

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ማኅበር በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ግልጽ እና ሕቡዕ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጠየቀ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሚያዝያ 27 2014 የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ማኅበር በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ግልጽ እና ሕቡዕ ጥቃቶች እንዲቆሙ የጠየቀው በዛሬው እለት ከሰሞኑ ማንነታቸው ባልተገለጸ የመንግስት ሰዎች ከመኖሪያ ቤቱ ተወስዶ የደረሰበት አልታወቀም የተባለው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ነው፡፡

ማኅበሩ ጋዜጠኛው ከቀናት በፊት ማንነታቸውን ባልገለጹ የመንግስት ሰዎች ተከራይቶ ከሚኖርበት ቤት ውስጥ ተይዞ መወሰዱንና የት እንዳለ አለመታወቁን ከሰማበት ጊዜ ጀምሮ መልስ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ በእጅጉ እንዳሳሰበው በመግለጫው አመልክቷል፡፡

አያይዞም ጋዜጠኛው በምን ጥፋት ተጠርጥሮ እንደተያዘና ምክንያቱ ምን እንደሆነ በግልጽ ካለመነገሩ በላይ የት እንደሚገኝ አለመታወቁ ከዚህ ቀደም በሌሎች ጋዜጠኞች ላይ የደረሰው መሰል ድርጊት አካል ሆኖ ማግኘቱን የገለጸ ሲሆን፣ ጋዜጠኞች በተደጋጋሚ ከሚሰሩበት ቦታ ወይም መኖሪያ ቤታቸው ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ በሚል በተመሳሳይ መልኩ ታፍነው የሚወሰዱበትና ደብዛቸው እንዲጠፋ የሚደረግበት ሁኔታ መደጋገሙ የሀገራችን የፍትሕ እና የዳኝነት ሥርዓቱ በራሱ የመገናኛ ብዙኃን ስጋት እንዲሆን አድርጎታል ብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎች ማኅበር በተለይ የማሕበሩ መስራች አባል የሆነው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ታፍኖ ተወስዶ እንዲሰወር የተደረገው የዓለማችን የፕሬስ ነጻነት ሳምንት በሚከበርበት ወቅት መሆኑ መንግስት በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በመገናኛ ብዙኃን ላይ ጥቃት እንደከፈተ እንደሚያስቆጥረው ገልጧል፡፡

ከሕግ አግባብ ውጭ መንግስትና በመንግስት ስም የሚንቀሳቀሱ ሕገ ወጥ ኃይሎች በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሱት ጥቃትም የሕዝብ አይንና ጆሮ የሆነውን ሚዲያ ሊያሸማቅቀው ቢችልም ይዋል ይደር እንጂ ራሱ መንግስትን ዋጋ የሚያስከፍለው መሆኑን መዘንጋት እንደሌለበት ጠቁሟል፡፡

መንግሥት ጋዜጠኞች ሥራቸውን በማከናወናቸው ብቻ ተጠያቂ የሚያደርግበትን ምስጢራዊ አሠራሩን ሊፈትሽ እንደሚገባ ያሳሰበው ማኅበሩ፣ ለመንግሥትም ሆነ በጠቅላላው ለአገር የሚፈይደው ነገር እንደማይኖር ይልቁንም መንግሥት እዘረጋዋለሁ ብሎ ከሚያምነው የዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ማሕበር ውጥኑ የሚቃረን ነው ብሎታል፡፡

በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሱ ግልጽና ሕቡዕ ጥቃቶች እንዲቆሙ በማሳሰብ፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ለምን በዚህ ሁኔታ እንደታሰረ፣ የት እንደሚገኝ እና የተያዘበት ምክንያት በግልጽ እንዲነገር ጠይቋል፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img