Saturday, November 23, 2024
spot_img

ኢሰመኮ በአፋር እና አማራ ክልሎች ያካሄደው የሰብአዊ መብቶች እና ዓለም አቀፍ የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች ላይ የተደረገ ምርመራ ሪፖርት ይፋ ሆነ

  • ኮሚሽኑ የትግራይ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን በሚችል መልኩ የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን ፈጽመዋል ብሏል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአፋር እና በአማራ ክልሎች ተስፋፍቶ በቆየው ጦርነት የተከሰቱ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በተመለከተ ከመስከረም ወር 2014 ጀምሮ ለአራት ወራት ያክል አድርጌዋለሁ ያለውን ምርመራ ባለ 110 ገፅ ሪፖርት ዛሬ መጋቢት 2፣ 2014 ይፋ አድርጓል፡፡

በዚህ ሪፖርቱ በአጠቃላይ 29 አባሎች የነበሩት የኢሰመኮ የምርመራ ቡድን፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች በጦርነቱ በተጎዱ በርካታ ቦታዎች በአካል በመገኘትና በተከታታይ የምርመራ ስልቶች ምርመራ ማከናወኑን የገለጸ ሲሆን፣ እነዚህም በአፋር ክልል ፈንቲ ረሱ እና አውሲ ረሱ ዞኖች የሚገኙ አካባቢዎችንና በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋ እና በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ የሚገኙ በአጠቃላይ 50 ስፍራዎችን ይጨምራሉ፡፡ የዚህ ምርመራ ዋነኛ ትኩረት በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ቢሆንም፤ በተወሰነ መጠን በትግራይ ክልል የተፈጸሙ የአየር ጥቃቶችን በሚመለከትም ኢሰመኮ ክትትል እና ምርመራ ማድረጉን አመልክቷል፡፡

ኮሚሽኑ በዚህ የምርመራ ሂደት በአጠቃላይ 427 ሚስጥራዊ ቃለ መጠይቆችን፣ ከልዩ ልዩ መንግሥታዊ መስሪያ ቤቶችና ኃላፊዎች ጋር 136 ስብሰባዎችን እና ከሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ከሃይማኖት መሪዎች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር 12 የቡድን ውይይቶችን ማድረጉን ገልጧል፡፡ ይህም ተጎጂዎችን፣ የተጎጂ ቤተሰቦችን፣ የየአካባቢው ነዋሪዎችንና የዓይን ምሰክሮችን፣ የሆስፒታልና ጤና ባለሙያዎችን፣ የእርዳታ ድርጅቶችንና፣ ሲቪል ማኅበራትን ይጨምራል ነው ያለው፡፡

ኮሚሽኑ በአንድ በኩል የትግራይ ኃይሎችና ተባባሪ ታጣቂዎች (በአንዳንድ አካባቢዎች የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ወይም በተለምዶ “ኦነግ ሸኔ” በመባል የሚጠሩትን ታጣቂ ኃይሎችን ጨምሮ) እና በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥት የፀጥታ ኃይሎች (የመከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የፀጥታ አባላት፣ የአማራና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎችንና ተባባሪ ሚሊሺያን ጨምሮ) አካቷል ያለው ጦርነት በአብዛኛው ሲቪል ሰዎች በሚኖሩባቸው የከተማ እና ገጠራማ አካባቢዎች በመካሄዱ በተሳታፊ ኃይሎች በተወሰዱ የኃይል እርምጃዎች ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሲቪል ሰዎች ሞተዋል፣ ለአካል እና ለሥነ ልቦና ጉዳት ተዳርገዋል፣ ፆታዊ እና ወሲባዊ ጥቃቶችም ተፈጽመውባቸዋል ብሏል። 

ኮሚሽኑ ምርመራ ባደረገባቸው አካባቢዎች ሆነ ተብለው የተፈጸሙ ሕገወጥ ግድያዎችን ሳይጨምር፣ በጦርነት ውስጥ በሲቪል ሰዎች ላይ በደረሰ የሕይወትና የአካል ጉዳት ብቻ ቢያንስ 403 ሲቪል ሰዎች ለሞት፤ እንዲሁም 309 ሲቪል ሰዎች ለቀላል እና ለከባድ የአካል ጉዳት ተዳርገዋል ብሏል፡፡

ኢሰመኮ ምርመራ ባደረገባቸው የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች በተለይም እና በዋነኝነት በትግራይ ኃይሎች ቢያንስ 346 ሲቪል ሰዎች በሕገወጥ መንገድ ተገድለዋል ያለ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተቆጣጠሯቸው ስፍራዎች በነበሩ የመንግሥት አስተዳደር ኃላፊዎች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ እንዲሁም መንግሥትን ይደግፋሉ ያሏቸው ሲቪል ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ግድያን መፈጸማቸውን አመልክቷል። በሌላ በኩል የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖ እና ሚሊሺያዎችም፤ የትግራይ ኃይሎች እና የኦነግ ሸኔ አባላት ወይም ደጋፊ ናቸው በሚል የጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ሕገወጥና ከዳኝነት ውጪ የሆኑ ግድያዎችን ፈጽመዋል፣ የአካል ጉዳትም አድርሰዋል ብሏል። 

የትግራይ ኃይሎች በአፋርና አማራ ክልሎች የሚገኙ ቦታዎችን ተቆጣጥረው በቆዩበት ጊዜ መጠነ ሰፊ፣ ጭካኔ የተሞላበትና ስልታዊ የሆነ በተናጠል እና በቡድን የተፈጸመ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት በሴቶች፣ በሕፃናት ሴቶችና አረጋዊያን ሴቶች ላይ አድርሰዋል ያለው ኮሚሽኑ፣ የትግራይ ኃይሎች ታጣቂዎች በሴቶች ላይ የፈጸሙት ፆታዊና ወሲባዊ ጥቃትን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለጦርነት ዓላማ እንዳዋሉት የሚያስረዳ ነው ብሎታል።

ኢሰመኮ የጦርነቱ ተሳታፊ ኃይሎች ዓለም አቀፍ ሰብአዊ መብቶችን እና የሰብአዊነት ሕጎችን ድንጋጌ በሚጥስ መልኩ የዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋ እና አስገድዶ መሰወር ፈጽመዋል ብሏል። የትግራይ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ወንጀልን እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊሆን በሚችል መልኩ የእገታ እና አስገድዶ መሰወር ተግባራትን የፈጸሙ መሆኑን አመልክቶ፣ የፌዴራል፣ የአማራ እና የአፋር ክልል የፀጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዐውድ ውስጥም ቢሆን የጥብቅ አስፈላጊነት፣ የተመጣጣኝነት እና ከመድልዎ ነፃ የመሆን መርሆዎች ከሚፈቅዱት ውጪ መጠነ ሰፊ የዘፈቀደ እስር ፈጽመዋል ብሏል፡፡

ኮሚሽኑ በሪፖርቱ በዝርዝር ባቀረባቸው መደምደምያዎችና ምክረ ሃሳቦች እንዳመለከተው፤ ምርመራው በተካሄደባቸው የአፋር፣ የአማራ እና የትግራይ ክልል አካባቢዎች የደረሱት የሰብአዊ መብቶችና የሰብአዊነት ሕግ ጥሰቶች በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆኑ የሚችሉ በመሆናቸው፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሰብአዊ መብቶች መርሆዎችን የተከተለ የወንጀል ምርመራ ሂደት ሊደረግ እንደሚገባ ገልጿል። ይህንንም ለማድረግና በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ ሁሉም ኃይሎች የተፈጸሙ ጥሰቶች ላይ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ የመጀመሪያው ኃላፊነት በመንግሥት ላይ የሚወድቅ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውሷል፡፡ 

እነዚህንና ከላይ የተጠቀሰውን የጣምራ ሪፖርት ምክረ ሃሳቦች ለማስፈጸም የዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡን ጨምሮ የሌሎች ሀገራዊ ተቋማት ሚና አስፈላጊ እንደሆነ የገለጹት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፣ “በቀዳሚነት በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች እና ኃይሎች በአባላቶቻቸው እና አመራሮቻቸው ለተፈጸሙ ከባድ የመብት ጥሰቶች ኃላፊነት መውሰድ እና ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ግዴታቸውን መወጣት ለፍትሕ፣ ለእውነት፣ ለተጎጂዎችና ለተጎጂዎች ቤተሰቦች የማይታለፍ እርምጃ መሆኑን በድጋሚ ሊታወስ ይገባል” ብለዋል።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img