Saturday, November 23, 2024
spot_img

የጤና ሚኒስቴር ከቀናት በኋላ የኮቪድ-19 የክትባት ዘመቻ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚያካሂድ አስታወቀ

የጤና ሚኒስቴር በኅዳር ወር 2014 ላይ ያካሄደው ዓይነት የኮቪድ-19 የክትባት ዘመቻ፣ ከተያዘው ጥር ወር መጨረሻ አንስቶ ለሁለተኛ ጊዜ እንደሚያካሂድ ገልጧል፡፡

ሚኒስቴሩ የኮቪድ-19 ክተባ በተፈለገው መጠን እየሄደ አለመሆኑን በመጥቀስ ከኅዳር 6፣ 2014 ጀምሮ ከሁለት ሳምንት በላይ የዘለቀ አገር አቀፍ የክትባት ዘመቻ አካሂዶ ነበር፡፡ በጎዳናዎች ጭምር ሲያካሂደው በሰነበተው የመጀመርያው የክትባት ዘመቻ፣ በ15 ቀናት ውስጥ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎችን መከተብ መቻሉን የሚኒስትሩ የብሔራዊ ክተባ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ዮሐንስ ላቀው ገልጸዋል፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለጻ በጤና ተቋማት ውስጥ ተገድቦ የነበረውን የክተባ ሒደት በዘመቻ መልክ ማስቀጠሉ እንደ ‹‹መልካም ተሞክሮ›› የታየ ሲሆን፣ ለዚህም ሲባል ይህን ዘመቻ ከቀናት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል፡፡ አቶ ዮሐንስ ‹‹እጃችን ላይ በቅርቡ ያገኘነው ወደ አሥር ሚሊዮን ዶዝ አለ፡፡ ይህን በዘመቻ ካልሰጠን በጤና ተቋማት ብቻ እየተሰጠ አይቀጥልም›› ብለዋል፡፡

እንዲህ ዓይነት ዘመቻዎች የሚካሄዱት ብዛት ያላቸው ሰዎችን በማንቀሳቀስ መሆኑን ያስታወሱት አቶ ዮሐንስ፣ ዘመቻ ማድረግ ቀላል የማይባል ጊዜና ወጪን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ለሁለተኛ ጊዜ የሚደረገው የክትባት ዘመቻ በአማካይ ከአሥር ቀናት ለማይበልጥ ጊዜ እንደሚቆይ አስታውቀዋል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የኮቪድ-19 ክትባትን መስጠት በጀመረበት ጊዜ ክትባቶቹን ማግኘት ፈተና ሆኖበት መቆየቱ የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ ከአመለካከትና ሌሎች ችግሮች የተነሳ የክተባ ሒደቱ እንደሚፈለገው እንዳልሆነ ተነግሯል፡፡ የአውሮፓውያኑ 2022 ከመግባቱ በፊት 20 ሚሊዮን ሰዎችን የመከተብ ዕቅድ ይዞ የነበረው የጤና ሚኒስቴር፣ እስካሁን መከተብ የቻለው 9.4 ሚሊዮን ሰዎችን ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ክትባቱን ሙሉ ለሙሉ የወሰዱት አራት ሚሊዮን ያህሉ ብቻ ናቸው ተብሏል፡፡

ጤና ሚኒስቴር አገር አቀፍ የክትባት ዘመቻዎችን ማካሄድ ክትባቱን በስፋት ለሕዝቡ ለመስጠት ካለው ጥቅም ባሻገር፣ ክትባቶቹ የአገልግሎት ጊዜያቸው እንዳያልፍ እየተጠቀመበት መሆኑን አቶ ዮሐንስ አስታውቀዋል፡፡ ከዚህ በፊት አዲስ አበባ ውሰጥ የክትባት ዘመቻ የተደረገው ሁለት ጊዜ መሆኑን አስታውሰው፣ በከተማዋ ዘመቻው ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው በከተማ አስተዳደሩ እጅ ያሉ ክትባቶች ‹‹ሊበላሹ ይችሉ›› እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት በነበረው አሠራር ወደ ኢትዮጵያ ሲላኩ የነበሩት የኮቪድ-19 ክትባቶች የአገልግሎት መጠቀሚያ ጊዜያቸው ሁለትና ሦስት ወራት እንደነበር ያሰረዱት አስተባባሪው፣ በዚህ የተነሳ ክትባቶቹ የአገልግሎት ጊዜያቸው ሊያልፍ ይችላል የሚል ሥጋት ተፈጥሮ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ከአራት ወራት ወዲህ መንግሥት የአገልግሎት ጊዜያቸው ከስድስት ወራት ያነሰ ክትባቶችን ላለመቀበል ወስኖ፣ በእዚያ እየተሠራ መሆኑን መግለጻቸውን የዘገበው ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img