Saturday, November 23, 2024
spot_img

በአዲስ አበባ ከሳዑዲ ተመላሽ የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ በርካቶች መታሰራቸው ተነገረ

አምባ ዲጂታል፣ ሐሙስ ሚያዝያ 21፣ 2013 ― በአዲስ አበባ ከተማ ከሳዑዲ አረቢያ ከስደት ተመላሾች የሚገኙበት በመቶዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች እየታሰሩ እንደሆነ የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች ነግረውኛል ብሎ ቢቢሲ አስነብቧል፡፡

እንደ ታሳሪ ቤተሰቦች ከሆነ በአዲስ አበባ ገላን ኮንደምኒየም እና ሐና ማርያም አካባቢዎች በሚገኙ እስር ቤቶች የታሰሩት የትግራይ ተወላጆች የእስራቸው ሰበብ ‹‹ብሔራቸው›› ነው፡፡

ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ በከተማው የትግራይ ተወላጆች እንደታሰሩ ቢያረጋግጡም፣ ምክንያቱ ብሔራቸው አለመሆኑን በመግለጽ ምክንያት ነው ያሉትን ተናግረዋል፡፡

‹‹ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ ሄደው ጦርነቱ አልሳካ ሲላቸው ተመልሰው ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የተለያዩ የሽብር ተግባራት የሚፈፅሙና ሕጋዊ ያልሆነ የጦር መሳርያ ይዘው የሚንቀሳቀሱ ብዙ ሰዎች አሉ›› ያሉት ኮማንደር ፋሲካ ፈንታ፣ ‹‹ሁሉንም ካሰርን እስር ቤትም አይበቃም። ስለዚህ በዋናነት ለዚህ ተግባር የሚያደራጁ፣ ገንዘብ የሚልኩ፣ ገንዘብ የሚያዋጡ፣ ጦርነቱ እንዳይቆም የተለያዩ ሥራ የሚሰሩና አገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች በተወሰኑ ቦታዎች አስረናል፤ ወደ ፍርድ ቤትም እያቀረብናቸው ነው›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የዜና ተቋሙ በተጨማሪ ከሳዑዲ ዐረብያ ተመልሰው በአዲስ አበባ ከተማ ታስረዋል ስለተባሉት የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲን አነጋግሬ ‹‹በጉዳዩ ላይ መረጃ የለኝም፤ ግን እዚህ ማንነት ላይ የተነጣጠረ ጥቃት የለም፤ እየተባለ ያለውን ነገር የተፈበረከ ሊሆን ይችላል›› የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል ብሏል፡፡

የታሳሪ ቤተሰቦች በበኩላቸው የታሰሩት የትግራይ ተወላጅ ወጣቶች፣ የእድሜ ባለፀጋዎች፣ ሴቶች እና ህፃናት እንዲሁም በቅርቡ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ ስደተኞች እንደሚገኙባቸው ይናገራሉ።

በአዲስ አበባ ከተማ የታሰሩትን የትግራይ ተወላጆች ጉዳይ በቅርበት እንደሚከታተል የተነገረለት የአውራምባ ታይምሱ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ እነዚህ በጅምላ ታስረዋል የተባሉ የትግራይ ተወላጆች በአራት እንደሚከፈሉ የገለጸ ሲሆን፣ እነዚህም ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ የመጡ፣ ከሳዑዲ አረቢያ የተመለሱ እና በትግራይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ገና ወደ ትግራይ ሳይሄዱ እዚህ አዲስ አበባ ታፍሰው የታሰሩ፣ በከተማዋ በተለያዩ የታችኛው መዋቅር በቀበሌ፣ በክፍለ ከተማና በሌሎች ሲሰሩ የነበሩ እንዲሁም ድንገት በቂም በቀልና በግል ጥላቻ ሰዎች ያሳሰሯቸው ናቸው›› ይላል።

በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች የትግራይ ተወላጆች እየታሰሩ እንደሆነ የሚገልፀው ጋዜጠኛ ዳዊት፣ ገላን ኮንዶሚንየም አካባቢ በሚገኘው ከቆርቆሮ በተሠራ መጋዘን ብቻ 736 ያህሉ ታስረው እንደሚገኙ ተናግሯል።

‹‹ከእነዚህ ወደ ውስጥ 70 በመቶ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው፤ 13 በመቶ ደግሞ ሴቶች ናቸው›› ብሏል ጋዜጠኛ ዳዊት።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አሮን ማሾ በበኩላቸው ኮሚሽኑ በጉዳዩ ላይ ማጣራት እየከናወነ እንደሚገኝ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ፎቶ፡ ታሳሪዎቹ ታጉረውበታል የተባለ ቤት

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img