አምባ ዲጂታል፤ ሐሙስ ሰኔ 30፣ 2014 ― መንግሥት ወደ ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ባለሥልጣናትን የላከው በኢትዮጵያ ቅርቡ የበርበራ ወደብን 19 በመቶ ድርሻ ማጣቷ መነገሩን ተከትሎ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የሶማሌላንዱን በርበራ ወደብ 19 በመቶ ድርሻ ወደቡን ከሚያስተዳድረው የዱባዩ ዲ ፒ ወርልድ ኩባንያ ጋር የተጋራችው በ2010 ነበር፡፡ በወቅቱ በተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች በተፈረመው ሥምምነት መሠረት ኢትዮጵያ 19 በመቶ ድርሻ ስትወስድ፣ ዲ ፒ ወርልድ የተባለው ዓለም አቀፍ የወደቦች አስተዳዳሪ ኩባንያ 51 በመቶ እና የሶማሌላንድ መንግሥት ደግሞ ቀሪውን 30 በመቶ ድርሻ ተጋርተዋል፡፡
ነገር ግን በተያዘው ሰኔ ወር መጀመሪያ ኢትዮጵያ በወቅቱ የተካፈለችውን ድርሻ ማጣቷን የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡ እንደ ዘገባዎች ከሆነ ኢትዮጵያ ድርሻውን ያጣችው በወቅቱ የተደረገውን ስምምነት ለማጠናቀቅ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ባለማሟላቷ ነው፡፡
ከመረጃው መውጣት በኋላ ኢትዮጵያ በ2010 ከዱባዩ ዲፒ ወርልድ እና ከሶማሌላንዱ ጋር የተጋራችውን የበርበራን ወደብ 19 በመቶ ድርሻ አጥታዋለች የሚባልበት ደረጃ ላይ እንዳልደረሰች የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ለመንግሥት ብዙኃን መገናኛዎች ገልጸው ነበር፡፡
አሁን ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገሥ ያሉበት ልዑክ ወደ ሶማሊላንድ ማቅናታቸው ተነግሯል፡፡ ልዑኩ ወደ ሶማሊላንድ ማቅናቱ ግን በይፋ አልተነገረም፡፡
ኢትዮጵያ በቅርቡ አጥታዋለች የተባለውን 19 በመቶ ድርሻ የበርበራ ወደብ ዲ ፒ ወርልድ እና ሶማሊላንድ እንደሚካፈሉት ተሰምቷል፡፡