Friday, April 26, 2024
spot_img

በጎንደር ከተማ የአካባቢውን ሙስሊሞች ዒላማ ባደረገ ድንገተኛ ጥቃት ቢያንስ የ25 ሰዎች ሕይወት ተቀጠፈ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ሚያዝያ 19፣ 2014 ― በጎንደር ከተማ ትላንት ሚያዝያ 18፣ 2014 ሸይኽ ከማል ለጋሥ የተባሉ የአገር ሽማግሌ ቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ የነበሩ የጎንደር ከተማ ሙስሊም ማኅበረሰብ አባላት ላይ በተከፈተ ድንገተኛ ጥቃት የ25 ሰዎች ሕይወት ተቀጥፏል፡፡

በከተማው በአራዳ ክፍለ ከተማ በተፈጠረው በዚሁ ጥቃት ከሞቱት ሰዎች በተጨማሪ በርካቶቹ አካላቸው ሲጎድል፣ የንግድ መደብሮች እና መስጂዶች ሲቃጠሉ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ተጋርተዋል፡፡

የክስተቱን መነሻ ምክንያት በተመለከተ በጉዳዩ ላይ መግለጫ ያወጣው የአማራ ክልል መጅሊስ «ወደ ጥንታዊ ሼህ ኤሊያስ መካነ-መቃብር ለቀብር በወጡ ሙስሊሞች ላይ በታጠቁ አክራሪ ክርስቲያኖች በቡድንና በነፍስ ወከፍ ትጥቅ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል» ብሏል።

የክልሉ መንግስት በበኩሉ ባወጣው መግለጫ ሥርዐተ ቀብር እየተፈጸመ በነበረበት ሰዓት ‹‹ከቀብር ቦታው ጋር ድንበርተኛ የኾነው ቤተ ክርስቲያን ላይ ለቀብር የሚሆን ድንጋይ ‹እናነሳለን የመስጊዱ ክልል ነው፤ አታነሱም የቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ነው› በሚል›› በተወሰኑ ግለሰቦች መካከል የተጀመረ ነው በሚል ሁኔታውን ገልጿል። ነገር ግን አምባ ዲጂታል ያነጋገራቸው የከተማው የዓይን እማኞች የክልሉ መንግስት ባወጣው መግለጫ ላይ የጠቀሰው ዐይነት ነገር እንዳልተከሰተ ገልጸዋል፡፡

የአይን እማኞቹ ‹‹ድንጋይ የሰረቀ፣ ድንበር የተሻገረም ሆነ መሳሪያ የታጠቀ ሰው በሙስሊሞቹ መካከል አልነበረም ያሉ ሲሆን፣ እኚሁ እማኝ ጥቃቱ በታቀደበት መልኩ በቤተክርስቲያን በተደራጁና በክልሉ መንግሥት በሚደገፉ ታጣቂዎች መፈጸሙን ገልጸዋል። የክልሉ እስልምና ም/ቤት በመግለጫው ‹‹እንደ ልባችሁ በተባሉ እና በመንግስት መዋቅር የሚደገፉ ኃይሎች ወንዝ ተሻግረው›› በእለቱ ሕይወታቸውን ያለፈ አባት ‹‹አናስቀብርም በማለት አስቀድመው ባዘጋጁት መሳሪያ ለቀብር በወጡ ሙስሊሞች ላይ በተኮሱት የመትረየስና የቦንብ ውርጅብኝ›› የሰዎች ሕይወት ማለፉን እንዲሁም ጉዳት እንደደረሰም ገልጧል።

ጥቃቱ የተፈጠረበት የጎንደር ከተማ አስተዳደር የጸጥታ ምክር ቤት ባወጣው ድርጊቱን ጥቃት ከማለት በተቆጠበበት መግለጫ ጥፋቱ የተፈፀመው ‹‹ጥቂት›› ባላቸው ‹‹ጽንፈኛና አክራሪ›› ግለሰቦች ነው ብሏል፡፡ የፀጥታ ምክር ቤቱ አክሎም ግጭት ብሎ የገለጸው ሁኔታ ‹‹የተከበሩትን የሁለቱን እምነት ተከታዮች ወደ ለየለት ግጭት ለማስገባት ሆን ተብሎ ለግጭት የማያበቃ ምክንያት በመምዘዝ ጥፋት እንዲፈጠር የተቀነባበረና የተመራ ሴራ›› ነው ሲል ገልጧል፡፡

ስለ ክስተቱ መነሻ ምንም መረጃ ያላሰፈረው የጎንደር ከተማ የፀጥታ ምክር ቤት፣ ‹‹እኩይ›› ሲል በገለጸው በዚህ ተግባር ከሁለቱም የእምነት ተከታዮች የህይወትና አካል መጉደል እንዲሁም የንብረት መቃጠልና ዘረፋ እንዳጋጠመ ቢያመለክትም፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ የጥቃቱ ሰላበ የሆኑት የከተማው እስልምና ሃይማኖት ተከታይ ነዋሪዎች ብቻ መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።

የፀጥታ ምክር ቤቱ ግጭቱን ቀስቅሷል በሚል በስም ያልጠቀሰው ቡድን ‹‹የፈለገው ጎንደርን ማቃጠል፣ መዝረፍና ማዋረድ›› ነበር ያለ ሲሆን፣ ‹‹ይህ ክፉ ተልዕኳቸው በፀጥታ መዋቅሩ፣ በሁለቱም የእምነት አባቶችና ወጣቶች እንዲሁም በሀገር ሽማግሌዎች ጥረት የፈለጉት ጥፋት ሳይደርስ መቆጣጠር›› እንደተቻለም ነው ያመለከተው፡፡

በከተማው በቀብር ሥነ ሥርዐት ላይ የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ ሕይወታቸው የተነጠቀውን ሰዎች ቁጥር በተመለከተ ትክክለኛው ቁጥር እስካሁን በክልሉ መንግስትም ሆነ በጎንደር ከተማ የፀጥታ ምክር ቤት የተጠቀሰ ነገር ባይኖርም፣ የአካባቢው ምንጮች የሟቾችን ቁጥር 25 አድረሰውታል።

ከግድያው በተጨማሪ በቁጥር 6 የሚደርሱ መስጂዶችና የአካባቢው ሙስሊም ነዋሪዎች ንግድ ሱቆች ላይ ጥቃትና ዘረፋ ተፈጽሟል። ከተቃጠሉት መስጂዶች ውጪ ‹‹መሳሪያ ደብቃችኋል›› ተብሎ መስጅዶች ሲፈተሹ ማደራቸውም የታወቀ ሲሆን «መፈክር» አስተጋብታችኋል›› በማለትም ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ሙስሊሞች ታስረዋል። ታስቦበትና ታቅዶበት የተፈጸመ ጠቃት እንደሆነ የሚገልጹት የከተማው ሙስሊም ነዋሪዎች በዚህ ጥቃት የጸጥታ አካላትና የመንግስት መዋቅሩ በቀጥታ ተሳታፊ ነበሩ ብለዋል።

ጥቃቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት እስካሁን በይፋ ያለው ነገር ባይኖርም፣ ግጭቱ በተሰማበት ወቅት በጠቅላይ ምክር ቤቱ የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ላይ ‹‹በጎንደር እየሆነ ያለውን ሙስሊሙን የማጥቃት፣ መስጂዶችን የመድፈር እና ንብረቶቹን የማውደም የተደራጀ ጥቃት እናወግዛለን›› የሚል ጽሑፍ አሥፍሯል፡፡

በጥቃቱ በርካቶች ቁጣቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ከነዚህ መካከል የሆኑት እውቁ የእስልምና ሃይማኖት መምህር አቡበከር አሕመድ ‹‹ብዙዎቹ ነገሮች ሁልጊዜ ለመስጠት እንደምንሞክረው ቀና መላምት፣ ለህዝቦች አብሮነት እንደምንለፋው ለመሸፋፈን የምንጥረው ነውር ራሱን ደግሞ ደጋግሞ እየገለጠ ነው›› በማለት ‹‹ይህን ነውር የጎንደር ህዝብ ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ሊጠየፈው ይገባል›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡

መምሕሩ አቡበከር ‹‹[የጎንደር ህዝብ] ከውስጡ የበቀሉ የነውረኛ ስብስቦችን ነቅሎ ለመጣል የሚከፈለውን ዋጋ ሁሉ ቢከፍል ለጎንደር ህዝብ የቆየ ሰላማዊነትና ለነገዋ ጎንደር እፎይታ እጅግ የሚገባ አንገብጋቢ ስራ ነው›› ብለዋል፡፡ አያይዘውም ‹‹የአካባቢው ባለስልጣናትና የክልሉ መንግስት አካባቢውን እና ክልሉን እረፍት የለሽ ሁከት ውስጥ እየከተቱ ክልሉን የነውረኞች መሸሸጊያ እንደሆነ የሚሰሩትን ሳያቃልል እና ምንም ምክንያት ሳይደረድር ሊያስቆምና ሊቀጣ ይገባል።

አመራሩ የሚወስደው የማያዳግም ርምጃ ለሰላሙ ብቻ ሳይሆን ነውረኞች በአመራሩ ውስጥ ሰርገው አለመግባታቸውን ማስተማመኛ የሚሰጥ›› እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ከጥቃቱ በኋላ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች ማለትም የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መግለጫ አውጥተዋል፡፡ ሁለቱም ፓርቲዎች ሁኔታውን ግጭት በማለት የገለጹት ሲሆን፣ በተፈጠረው «ግጭት» የሰው ሕይወት በመቀጠፉ ሐዘኑን የገለጸው ኢዜማ፣ ‹‹ሀገር የሁላችን ናት፡፡ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እና ከልካይ ምክንያት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መብታቸው ተከብሮ ሊኖሩ ይገባል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁንም ክቡር የሰው ህይወት እንደዘበት የሚቀጠፍባት ሀገር እንደሆነች ቀጥላለች›› ብሏል፡፡

ጨምሮም ‹‹በተቀናጀ ሁኔታ የሀገርን እና ህዝቧን ደህንነት ለማስጠበቅ መስራት አስቸኳይ እና አንገብጋቢ አጀንዳው እንዲሆን›› ሲል መንግስትን አሳስቧል፡፡ ጉዳዩ በፍጥነት ተጣርቶም መንግስት አጥፊዎችን ለፍርድ እንዲያቀርብ እንዲሁም ችግሩ እንዳይስፋፋ እና የበለጠ ጥፋት እንዳያመጣ እንዲቆጣጠር ፓርቲው ጠይቋል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ በበኩሉ የጎንደር ከተማ ሙስሊምና ክርስቲያን ወገኖቻችንን ለማፋጀት ተጀምሯል ያለውን እንቅስቃሴ ሁሉም የማኅበረሰባችን ክፍል ‹‹ተባብሮ ሊያስቆመው ይገባል›› ብሏል፡፡

ፓርቲው በስም ያልጠቀሳቸውንአካላት ይህ አጀንዳ ‹‹ሕዝባችንን ማኅበራዊ እረፍት መንሳት የሚፈልጉ አካላት አጀንዳ መሆኑን በመረዳት የጎንደር ሙስሊምም ሆነ ክርስቲያን ነዋሪዎች ግጭት ከሚያባብሱ እንቅስቃሴዎች በመታቀብ አጥፊዎችን መቆጣጠር ላይ በትኩረት ርብርብ እንዲያደርጉ›› ሲል ፓርቲው ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

ትላንት በቀብር ሥነ ሥርዐታቸው ላይ ሁከት የተፈጠረው ሸይኽ ከማል ለጋሥ ላለፉት 40 ዓመታት በማኅበራዊ አገልግሎት፣ በባህላዊ እና መንፈሣዊ ህክምና የሚታወቁ እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡ እኚህ የአገር ሽማግሌ በከተማው በእስልምናም ሆነ በክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ የሚከበሩ እንደነበሩም ነው የተነገረው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img