አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ሚያዝያ 12፣ 2014 ―በኢትዮጵያ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን 83 በመቶ ድርሻ የተመሠረተው የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር፣ በአፋር ክልል አፍዴራ የተሰጠው የጨው ማምረት ፍቃድ እንዳይታደስ የአፋር ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አወል አርባ ጠይቀዋል፡፡
የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ አወል ጥያቄውን ያቀረቡት ለማዕድን ሚኒስቴር ሲሆን፣ ምክንያት አድርገው ያቀረቡት ደግሞ የአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር ላለፉት ሃያ ዓመታት በአፋር ክልል ጨው ለማምረት ሲጠቀምበት የነበረው የማዕድን ፈቃድ በመጪው ሰኔ 2014 እንደሚጠናቀቅ በማመልከት ነው፡፡
አቶ አወል ለአክስሲዮን ማኅበሩ የተሰጠው የማዕድን ፍቃድ ጊዜ ሲጠናቀቅ ይዞታው ለክልሉ እንዲመለስ፣ በይዞታው ላይ ጨው የማምረት አዲስ የማዕድን ፈቃድ ለአፋር ልማት ድርጅት እንዲሰጥ ጥያቄያቸውን አቅርበዋል።
የፌዴራል መንግሥት የልማት ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ የማዕድን፣ ነዳጅና ባዮፊውል ኮርፖሬሽን በአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር ላይ 83 በመቶ ድርሻ በመያዝ ወሳኝ ባለድርሻ ሲሆን፣ ቀሪው 17 በመቶ የሕወሓት ኢንዶውመንት የሆነው ኢፈርትና ሌሎች ባለ ድርሻዎች የተያዘ መሆኑን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ በአፋር ክልል አፍዴራ በ1 ሺሕ ሔክታር ላይ የሚገኝ የጨው ክምችትን ለማምረት፣ የዛሬ ሃያ ዓመት የማዕድን ፍቃድ ማግኘቱን ለመረዳት ተችሏል።
ይሁን እንጂ የአክሲዮን ማኅበሩ ይዞታ በተለያዩ ምክንያቶች ተሸርሽሮ፣ በአሁኑ ወቅት በ300 ሔክታር ይዞታ ላይ ብቻ ጨው እያመረተ እንደሚገኝ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
የአክሲዮን ማኅበሩ ጨው ለማምረት የተሰጠው የሃያ ዓመት ፍቃድ በመጪው ሰኔ ወር 2014 እንደሚያበቃ የተገነዘበው የአፋር ክልል መንግሥት፣ የአክሲዮን ማኅበሩ ፍቃድ እንዳይታደስ ያቀረበው ጥያቄ፣ በክልሉ ከሚገኘው ጨው ሀብት የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ አለበት የሚል ነው።
የክልሉ ርእሰ መስተዳደር አቶ አወል ለማዕድን ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ ‹‹በአፋር ጨው አክሲዮን ማኅበር ላለፉት ሃያ ዓመታት የተያዘው የጥሬ ጨው ማምረቻ ቦታ ለክልሉ ልማት፣ በተለይም ለሕዝቡ ምንም ዓይነት ፋይዳ ሳይሰጥ የክልሉ ሕዝብ ያለው አንዱ ሀብት ጨው ሆኖ ሳለ የበይ ተመልካች ሆኖ ቆይቷል›› ሲሉ ገልጸዋል።
ርእሰ መስተዳደሩ በዚሁ ደብዳቤ፣ ‹‹በአሁኑ ወቅት የብልፅግና መንግሥት›› ለክልሎች እየሰጠ ባለው ከፍተኛ ድጋፍ በአፋር ክልል ከእንስሳት እርባታና ግብርና ቀጥሎ በማዕድን ሥራዎች ላይ የክልሉን ወጣት በማደራጀት፣ ወጣቱን የልማቱና የዕድገቱ አካል ለማድረግ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ውስጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
‹‹ስለሆነም በሰኔ ወር 2014 የሚያበቃው የአፋር ጨው አክሲዮን ማኅበር ማምረቻ ቦታ ለአፋር ልማት ይወል ዘንድ ለአፋር ልማት ማኅበር እንዲተላለፍ፤›› ሲሉ ለማዕድን ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ ጠይቀዋል።
የአክሲዮን ማኅበሩ አመራሮች ሰኞ ሚያዝያ 10፣ 2014 ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ተወያይተዋል ነው የተባለው፡፡
ይሁን እንጂ የአክሲዮን ማኅበሩ የሥራ ኃላፊዎች በክልሉ መንግሥት ስለቀረበው ጥያቄ መረጃው ቢኖራቸውም፣ ጉዳዩ ጥንቃቄን የሚሻ እንደሆነ በመግለጽ ማብራሪ ከመስጠት ተቆጥበዋል የተባለ ሲሆን፣ የአክሲዮን ማኅበሩ የንግድ መምርያ የሥራ ኃላፊ የሆኑት አቶ ተስፋዬ አበራ ግን ‹‹በእኛ በኩል የፈቃድ ዕድሳት ጥያቄ አቅርበናል›› ማለታቸው በጋዜጣው ዘገባ ተመላክቷል፡፡
የፍቃድ ዕድሳት ጥያቄ ቀርቦ መሟላት የሚገባቸውን በማሟላት ሒደት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት በአፋር ጨው ማምረቻ አክሲዮን ማኅበር ላይ ያለውን 83 በመቶ ድርሻ የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ማዕድን ነዳጅና ባዮፊዩል ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ ይህ ኮርፖሬሽን በ16.7 ቢሊዮን ብር የተፈቀደ ካፒታል በ2012 በድጋሚ የተቋቋመ ነው፡፡