Saturday, November 23, 2024
spot_img

ኢትዮጵያውያኑ ጋዜጠኞችና የሚዲያ ባለሞያዎች የታሠሩ የሞያ ባልደረቦቻቸው እንዲለቀቁ ጠየቁ

በቁጥር 16 የሆኑ ነዋሪነታቸውን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገራት ያደረጉ ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች፣ በአሁኑ ጊዜ በእስር ቤት የሚገኙ የሞያ ባልደረቦቻቸው እንዲለቀቁ በጋራ ባወጡት መግለጫ ጠይቀዋል፡፡

ይኸው የጋዜጠኞች ስብስብ፣ በጋዜጠኝነት ሥራቸው ብቻ ኢላማ የተደረጉ ናቸው ያላቸውን በሥም ያልዘረዘራቸውን ጋዜጠኞች ነው እንዲለቀቁ የጠየቀው፡፡

ስብስቡ አፍሪካን አርጊዩመንትስ በተሰኘ ድረ ገጽ ባስነበበው የአቋም መግለጫው፣ በኢትዮጵያ ባለፉት አስርት ዓመታት በጋዜጠኞች ላይ ሲካሄድ የነበረውን እንግልት አንስቷል።

ኢትዮጵያም ላለፉት በርካታ ዓመታት ከዓለማችን ጋዜጠኞችን አሳሪ አገራት ተርታ እንደነበረች ያስታወሰው ስብስቡ፣ በቅርብ ዓመታት በተለይ በሥራ ላይ የዋለው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ለጋዜጠኞች ፈተና ሆኖ ማለፉን አመልክቷል፡፡ ይኸው አዋጅ ጋዜጠኞች በሀገር ክሕደት እና ሽብር ተከሰው ለእድሜ ልክ እስር እንዲዳረጉ ጥርጊያ የሚከፍት እንደነበርም ጠቅሷል።

አዋጁ ለበርካታ ጋዜጠኞች እስር እና ስደት ሰበብ መሆኑን የጠቀሱት ጋዜጠኞቹ፣ የመንግሥትን አጀንዳ የማያስተጋቡ የብዙኃን መገናኛዎችም እንዲዘጉ አድርጓል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በ2010 በመጣው የፖለቲካ ለውጥ የታሰሩ ጋዜጠኞች መፈታታቸውን፣ በስደት አገር የነበሩ እንዲመለሱ ጥሪ መደረጉን፣ በውጭ አገራት መቀመጫቸውን ያደረጉ ብዙሃን መገናኛዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በአገር ውስጥ ቢሮ መክፈታቸውን በማስታወስ፣ በወቅቱ ኢትዮጵያ በአስርተ ዓመታት ታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጠኞች ያልታሰሩባት አገር ሆና እንደነበርም ገልጿል፡፡

ሆኖም ይህ የነጻነት ዐየር ተቀልብሶ ኢትዮጵያ ዳግም ጋዜጠኞች የሚታሰሩባት እና የብዙሃን መገናኛዎችም ተገደው የሚዘጉባት አገር መሆኗን የገለጸው ስብስብ፣ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት ቢያንስ 40 ጋዜጠኞች ወደ እስር ቤት ተወረውረው ኢትዮጵያም ወደ ቀደመ የአሳሪነት ታሪኳ ተመልሳለች ብለዋል፡፡

እነዚህ ጋዜጠኞች ኢትዮጵያ ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ጋዜጠኞችን አስመልክቶ ያስመዘገበችው መልካም ሥም ወደ ኋላ በመመለሱ ቁጭት እና ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

ሥማቸው የተጠቁሱት 16 ጋዜጠኞች እና ከሚሰሩባቸው ሚዲያዎች ፍቃድ ባለማግኘት ምክንያት ሳይካተቱ የቀሩ ጋዜጠኞች በአቋም መግለጫቸው፣ በቅርብ ሳምንታት የተወሰኑ ጋዜጠኞች ከእስር መለቀቃቸውን በበጎ እንደሚመለከቱ የገለጹ ሲሆን፣ አሁንም በመላው ኢትዮጵያ በእስር ቤት ያሉ ቀሪ ጋዜጠኞች በአፋጣኝ እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል።

ጋዜጠኞቹ በዚሁ መግለጫ ላይ እንደ ሲፒጄ እና ድንበር የለሹን የጋዜጠኞች ቡድን፣ ከታሳሪ ጋዜጠኞች ጎን በመቆማቸው ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።

እነዚህ ጋዜጠኞች ርዕዮት ዓለሙ፣ ዐብዱረዛቅ ሸይኽ ሐሰን፣ አርጋው አሽኔ፣ ሙኒራ ዐብዱልመናን፣ አክመል ነጋሽ፣ ዳዊት እንደሻው፣ ደጀኔ ጉተማ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ እሸቴ በቀለ፣ ቃልኪዳን እጅጉ፣ ማያ ምስክር፣ ሳዲቅ ከድር፣ ሺመልስ መረሳ፣ እያስጴድ ተስፋዬ፣ ጸዳለ ለማ እና ዘካሪያስ ዘላለም ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ባለፈው ጥቅምት ወር የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተከትሎ በርካታ ጋዜጠኞች እና የሚዲያ ባለሞያዎች መታሰራቸው ይታወቃል።

ከነዚህ መካከል የተራራ ኔትወርኩ ታምራት ነገራ፣ የአሶሽየትድ ፕረስ ዘጋቢው አሚር አማን እና የካሜራ ባለሞያው ቶማስ እንግዳ አሁንም በእስር ቤት ይገኛሉ።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img