Saturday, November 23, 2024
spot_img

ምርጫ ቦርድ የኦነግ ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ የሚገኙበት የቤት ውስጥ እስር በአፋጣኝ መቆም አለበት አለ

አምባ ዲጂታል፤ ዐርብ የካቲት 25 2014 ― የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የቤት ውስጥ እስር እንዲቆም የጠየቀው፤ ጉዳዩን አስመልክቶ ለፌደራል ፓሊስ ኮሚሽን እና ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት መስሪያ ቤቶች በጻፈው ደብዳቤ ነው፡፡

ቦርዱ በጻፈው ደብዳቤ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን አቤቱታ የሚያጣራ ቡድኖች መቋቋሙን የገለጸ ሲሆን፣ በዚህ የማጣራት ሒደት የኦሮሚያ ክልል አጣሪ ቡድን የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመጋቢት 24፣ 2013 አንስቶ ከቤታቸው እንዳይወጡ ተደርገው የቁም እስረኛ እንደሆኑ አቤቱታ መቅረቡን አመልክቷል፡፡

ይህንኑ አቤቱታ ተከትሎ የሚያጣሩ ሁለት አካላት ወደ አቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት የካቲት 21፣ 2014 በመሄድ አቶ ዳውድ ያሉበትን ሁኔታ መመልከታቸውንም ነው የገለጸው፡፡

ቦርዱ እንዳለው፣ አጣሪዎቹ በሪፖርታቸው የሊቀመንበሩ መኖሪያ ቤት ሲደርሱ አንኳኩተው የከፈቱላቸው ሲቪል የለበሱ የፀጥታ ሰራተኞች መሆናቸውንና ማንም ሰው መግባት እንደማይፈቀድለት ገልፀው፣ ገብተው ለማየት መጀመሪያ ፍቃድ መጠየቅ ያለበት መሆኑን ከየት እንደመጡና ለምን እንደመጡ በመጠየቅ በመጨረሻ እንዲጎበኟቸው ተፈቅዷል፡፡  

ጨምሮም የቡድኑ አባላት ከአቶ ዳውድ ኢብሳ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት የያዙት ቦርሳ መፈተሹን እንዲሁም ስልካቸውን ይዘው መግባት እንደማይችሉ እንደተገለፀላቸውና በመጨረሻም ይህን ፈፅመው ከአቶ ዳውድ ጋር እንደተገናኙ ለቦርዱ ሪፖርት አቅርበዋል ብሏል።

የአጣሪ ቡድኑ አባላት ከአቶ ዳውድ ጋር ባደረጉት ውይይትም ከመጋቢት 24፣ 2013 ጀምሮ ከቤት እንዳይወጡ የታጠቁ ሰዎች ግቢያቸው ውስጥ ተመድበው የከለከሏቸው መሆኑን ገልጸዋል ያለው ቦርዱ፣ በዚህም አቶ ዳውድ ኢብሳ የቤት ውስጥ እስረኛ ሆነው የመንቀሳቀስ መብታቸው እንደተገደበ ተገንዝቤያለሁ ነው ያለው፡፡

ምርጫ ቦርድ በደብዳቤው ማሳረጊያ እኚህ የፓርቲ አመራር በየትኛውም የህግ አግባብ ተቀባይነት በሌለው ሁኔታ የሚገኙበትን የቤት ውስጥ እስር በአፋጣኝ መቆም እንዳለበት ያስገነዘበ ሲሆን፣ ተቋማቱ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ግቢ የመደቡትን ጥበቃ እንዲያነሱና የሊቀመንበሩን የመንቀሳቀስ መብት አስከብረው በአስቸኳይ ለቦርዱ እንዲገልጹም አሳውቋል።  

 

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img