Sunday, September 22, 2024
spot_img

አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ያልጣለችው ተፋላሚ አካላት ግጭቱን በንግግር ከፈቱት ጊዜ ለመስጠት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ገለጹ

አምባ ዲጂታል፣ ዐርብ ኅዳር 3፣ 2014 ― በዛሬው እለት ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተገናኘ ተሳትፎ አላት በሚል ኤርትራ ላይ ማዕቀብ የጣለችው አሜሪካ፣ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት እና በሕወሓት ላይ ማዕቀብ ያልጣለችው ሁለቱ አካላት ግጭቱን በንግግር ከፈቱት ጊዜ ለመስጠት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ አንቶንዮ ብሊንክን ገልጸዋል።

ከሰሞኑ የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ የፌዴራል መንግስት እና ሕወሓትን ለማሸማገል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የደገፈችው አገሪቱ፣ በተፋላሚ አካላት መካከል ከንግግር ጋር በተገናኘ ለውጥ የማይመጣ ከሆነ ማዕቀቡን ለመጣል መዘጋጀቷን አሳውቃለች።

አንቶንዮ ብሊንክን ይህን ያሳወቁት በዛሬው እለት የአገሪቱ ግምጃ ቤት የውጭ ሐብት ቁጥጥር ቢሮ ዛሬ ይፋ ባደረገው አገራቸው የኤርትራን ገዢ ፓርቲ ሕግዴፍ እና ጦሩን ጨምሮ በባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ መጣሏን በገለፁበት ወቅት ነው።

ግምጃ ቤቱ ባወጣው መግለጫ ላይ ማዕቀቡ ከኤርትራው ገዢ ፓርቲ ሕዝባዊ ግንባር ለዴሞክራሲ (ሕግዴፍ) እና ጦሩ በተጨማሪ የኤርትራ ብሔራዊ ደህንነት ቢሮ ሃላፊ አብርሃ ካሳ ነማርያም እና የፓርቲው የኢኮኖሚ ጉዳዮች አማካሪ ሐጎስ ገብረህይወት አካቷል።

ከነዚሁ ግለሰቦች ጋር ተያይዞም ሐጎስ በዋና ስራ አስፈፃሚነት የሚመሩት ሬድ ሲ ትሬዲንግ እና የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ፓርቲ የንግድ ተቋማትን በበላይነት የሚያስተዳድረው ህድሪ ትረስት የተሰኘ ድርጅት ማዕቀቡ ተጥሎባቸዋል።

ግምጃ ቤቱ ሁለቱ ድርጅቶች ላይ ማዕቀብ በመጣሉ፣ በአሜሪካ ውስጥ የሚገኝ ሐብታቸውን ከማንቀሳቀስ ታግደዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጋር በተያያዘ ለሰላምና መረጋጋት እንቅፋት በሚሆኑ፣ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦትን ወይም የተኩስ አቁም እንዳይደረግ በሚያደናቅፉ እንዲሁም ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በሚፈጽሙ ግለሰቦችና አካላት ላይ ማዕቀብ ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ በመስከረም ወር አጋማሽ መፈረማቸው አይዘነጋም።

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img