Monday, October 7, 2024
spot_img

የአማራ ክልል የሕወሓትን ትንኮሳ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን የክልሉ ርእሰ መስተዳደር ተናገሩ

አምባ ዲጂታል፣ ማክሰኞ ሰኔ 29፣ 2013 ― የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ክልሉ ከሕወሓት የሚፈፀምበትን ትንኮሳ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የገለፁት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ ነው።

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ እየተሰራ መሆኑን በገለጹበት መግለጫ፣ የህወሓት ቡድን የሚፈፅመው ትንኮሳን ለመመከት ግን የአማራ ክልል ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል።

ከህወሓት ሊሰነዘር የሚችል ማንኛውንም ዐይነት ጥቃት ለመመከት ሙሉ አቅም እና ዝግጁነት አለን ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ በተለይ ልዩ ኃይሉ እና ሚሊሻው ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር መንግስት የወሰነው የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ በተራዘመ ግጭት የሚመጣውን ችግርና ጫና ያስቀረ ነው ማለታቸውን የመንግሥት ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡

የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ በተመሳሳይ በትላንትናው እለት ከትግራይ ክልል ጋር የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸውና በቅርቡ በትግራይ በነበረው ጦርነት በአማራ ልዩ ኃይል ቁጥጥር ስር የዋሉት የወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምትና ራያ ጉዳይ ፋይሉ የተዘጋ ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

የርእሰ መስተዳደሩ ንግግር የመጣው ከቀናት በፊት የሕወሃት አመራሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ኤርትራና አማራ ክልል ድረስ በመግባት ‹‹ጠላት›› ያሏቸውን እንደሚዋጉ መናገራቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተገናኘ መረጃ የሕወሃት ኃይሎች የአጎራባች የአማራ ክልል ሚሊሻዎችን ለመፋለም መንቀሳቀሳቸውን ዘ ጋርዲያን ይዞት በወጣው ዘገባ አመልክቷል፡፡

የሕወሃት ኃይሎች ከሳምንት በፊት የአገር መከላከያ ሠራዊት መቀሌን መያዙን ተከትሎ የክልሉን በርካታ አካባቢዎች ዳግም መያዛቸው መነገሩ አይዘነጋም፡፡

ዘ ጋርዲያን ከዓይን እማኞች ሰማሁ እንዳለው የሕወሃት ኃይሎች አሁን ወደ ክልሉ ምዕራባዊ አቅጣጫ የዘመቱት በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ ወዶ ዘማቾችን አስከትለው ነው፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img