Monday, September 23, 2024
spot_img

ኢዜማ በቅርቡ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ወረዳ ፍርድ ቤትን በተመለከተ ማብራሪያ ጠየቀ

– ፓርቲው የተቋቋመው ፍርድ ቤት የሕግ መሠረት የሌለው ነው ብሏል

አምባ ዲጂታል፣ ቅዳሜ ግንቦት 28፣ 2013 ― የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በቅርቡ የተቋቋመው የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ወረዳ ፍርድ ቤት ሥልጣን እና ተግባራት ላይ ማብራሪያ ይሰጠኝ ሲል የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ጠይቋል፡፡

ኢዜማ ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በላከው ደብዳቤ፣ በተለያዩ መንግሥታዊና የግል ሚዲያዎች ‹‹የፊንፊኔ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት›› በይፋ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀመረ በማለት የተሰሩት ዘገባዎች፣ በሕገ መንግሥቱ ለአዲስ አበባ ከተማ የተሰጠውን ራስን በራስ የማስተዳደር ሥልጣን የሚጋፋ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡

ፓርቲው በፍርድ ቤቱ መከፈት ወቅት በተሠራው የሚዲያ ዘገባ የአዲስ አበባ ዙሪያ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ኩመላ ቡላ «በፊንፊኔ ከተማ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችም ሕገ መንግሥታዊ መብታችውን በመጠቀም በዚህ ፍርድ ቤት በቋንቋቸው የመዳኘትና ተደራሽ የሆነ የፍትህ አገልግሎት የማግኘት መብትም ያገኛሉ» ማለታቸውን በማስታወስ፣ ይህንኑ ተከትሎ አዲስ የተከፈተው ፍርድ ቤት ሥልጣንና ተግባራት ላይ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግን ማብራሪያ ጠይቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለሚገጥማቸው ማናቸውም ጉዳይ የትኛውም ብሔር ጀርባ ቢኖራቸውም የመዳኘት ሥልጣኑ የከተማ መስተዳደሩ ፍርድ ቤቶችና የፌደራል ፍርድ ቤቶች መሆኑን የጠቀሰው ኢዜማ፣ አንድ ክልል የዚህ ብሔር ተወላጆችን ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም የመዳኘት ሥልጣን ይኖረኛል ማለቱ በሕገ መንግሥቱ ለፌደራል መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣን የሚጋፋ፤ በአዲስ አበባ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 87/1989 እንዲሁም እሱን ያሻሻለው አዋጅ ቁጥር 361/1995 የአዲስ አበባ አስተዳደር ራስ ገዝ ከመሆኑም ባሻገር በፌደራሉ መንግሥት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን ሥር በማይወድቁ ጉዳዮች ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤቶች አና የቀበሌ ማኅበራዊ ፍርድ ቤቶች ብቻ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ተብሎ የተደነገገውን በግልጽ የሚቃረን ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡

በተጨማሪም አሁን ለተቋቋመው ፍርድ ቤት የሕግ መሰረት ተደርጎ የተጠቀሰው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አደረጃጀት ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 216/2011 በአንቀጽ 24 ላይ ከተዘረዘሩት የኦሮሚያ ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸው ሥልጣን እና ተግባራት ላይ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት ሥልጣን እንዳላቸው ባልጠቀሰበት ሁኔታ፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆችን ጉዳይ የማየት የዳኝነት ፈቃደ ሥልጣን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፍርድ ቤቶች አላቸው ተብሎ መገለጹ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እና ምንም ዓይነት የሕግ መሰረት የሌለው ነው ብሎታል፡፡

በጉዳዩ ላይ ዐቃቤ ሕግ እስካሁን ድረስ በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም፡፡

ተዛማጅ ጽሑፍ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

ትኩስ ርዕስ

- Advertisment -spot_img